በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታንዛኒያ የሚገኙ ቡሩንዲያውያን ስደተኞች ሥጋት


ሁለት መቶ ሺህ ቡሩንዲያውያን ስደተኞችን በመጪው ጥቅምት ወር ከታንዛኒያ ወደሃገራቸው መመለስ ለመጀመር የተደረሰው ስምምነት በስደተኞቹ ዘንድ ስጋት ፈጥሯል። ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቤቱታ እናቀርባለንም ብለዋል፡፡ ቢያንስ አንድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ስደተኞቹ በግድ ቢመለሱ እከሳለሁ ብሏል።

ምዕራብ ታንዛንያ የሚገኘው ኢንዱታ ካምፕ የተጠለሉት ሪኖቫት እንዱዋዮ የሚባሉ ስደተኛ የታንዛንያ መንግሥት ከቡሩንዲ መንግሥት ጋር ተባባሮ በግድ ሊመልሰን እንደሆነ ግልጽ ነው ብለዋል።

የታንዚንያ የሀገር ግዛት ሚኒስትርና የቡሩንዲ አቻቸው የፈረሙት ሥምምነት ዕሁድ ዕለት ይፋ ሆኗል። በሳምንት ሁለት ሺህ ስደተኞች ይመለሳሉ ነው የተባለው።

የታንዛንያው የሀገር ግዛት ሚኒስትር ሉጎላ ሲናገሩ ሁለቱ መንግሥታት ተደራደረው ስምምነቱ ላይ የደረሱት የቡሩንዲ የፀጥታ ሁኔታ አርኪ ደረጃ ላይ መሆኑን ስላመኑ ነው ብለዋል። ስደተኛው ግን ፀጥታው አልተሻሽለም አብዛኞቻችን መመለስ እንፈልግም ብለዋል። ከዜና ዘገባዎች የምንሰማው ሰዎች እንደሚገደሉ የደረሱበት እንደሚጠፋ ከህግ ውጭ እንደሚታሰሩ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ባለፈው ሰኔ ወር ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት፣ የቡሩንዲ ባለሥልጣናት እና የገዢው ፓርቲ ወገን የሆኑ ወጣቶች፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ቡድን አባላትን ናቸው ተብለው የጠረጠሩዋቸውን በርካታ ሰዎች ደብደባዋል፣ ገድለዋል፣ በዘፈቀደ አስረዋል፣ ደብዛቸውን አጥፍተዋል ሲል ወንጅሉዋል። የታንዛኒያ መንግሥት አስገድዶ የሚመልሰን ከሆነ የተመድ የስደተኞች ኮሚሽነር ወደሌላ የምስራቅ አፍሪካ ሃገር እንዲያዛውረን እንጠይቃለን ብለዋል ስደተኛው።

/ዩኤንኤችሲአር/ ስለሁለቱ ሃገሮች ስምምነት እስካሁን አስተያየት አልሰጠበትም። የቡሩንዲ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሰለባዎች ተሟጋች ጠበቆች ህብረት የተባለ ድርጅት የታንዛንያን መንግሥት በዓለምቀፍ ፍርድ ቤቶች እንከሰዋለን ሲል አስታውቋል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG