በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቡርኪናፋሶ 'ለ ሞንድ' የተሰኘውን የፈንሳይ ዜና ማሰራጫ አገደች


የፈንሳይ እለታዊ የዜና ማሰራጫ 'ለ ሞንድ'
የፈንሳይ እለታዊ የዜና ማሰራጫ 'ለ ሞንድ'
የፈንሳይ እለታዊ የዜና ማሰራጫ 'ለ ሞንድ' በሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ በደረሰ የጂሀድ ጥቃት ላይ ያወጣውን ፅሁፍ ተከትሎ፣ በወታድራዊ አገዛዝ የምትመራው ቡርኪናፋሶ፣ ቅዳሜ እለት ሁሉንም የለ ሞንድ ማከፋፈያ መንገዶች አግዳለች።
የሀገሪቱ ኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር ሪምታልባ ጂን ኢማኑኤል ኡድራጎ ባወጡት መግለጫ "በቡርኪና ፋሶ የሚገኘው ለ ሞንድ ጋዜጣ የሚከፋፈልባቸው ሁሉም መንገዶች ከቅዳሜ ኅዳር 22፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ እንዲታገድ መንግስት ወስኗል" ብለዋል።
ጂቦ በተሰኘ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ኅዳር 16 ቀን በደረሰው ጥቃት ዙሪያ ለ ሞንድ ድህረ ገፅ ላይ "አድሏዊ ፅሁፍ" መታተሙን በመጥቀስም ሚዲያውን ተችተዋል።
የእስልምና እና የሙስሊሞች ድጋፍ ቡድን ኃላፊነቱን በወሰደበት ጥቃት ቢያንስ 40 ንፁሃን ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን የቡርኪናቤ ደህንነት ምንጮች ጥቂት ወታደሮች መሞታቸውንም ተናግረዋል።
"ለ ሞንድ ጋዜጣ ካለው በተቃራኒ፣ የቡርኪናቤ መንግስት በፀረ-ሽብርተኝነት ላይ በሚያካሂደው ጦርነት እራሱን በፕሮፓጋንዳ አስተሳሰብ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶ አያውቅም" ብለዋል ኦድራጎ።
የቡርኪናቤ ባለስልጣናት በቅርብ ወራት ውስጥ የፈረንሳይ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ኤል ሲ አይ እና ፍራንሲ 24ን፣ እንዲሁም ራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል እና ዠን አፍሪክ መጽሔትን አግደዋል። የሊብሬሽን እና የለ ሞንድ ጋዜጦች ዘጋቢዎችንም ከሀገር አባረዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሚያዚያ ወር ባወጣው ሪፖርት፣ ባለስልጣናት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር የፕሬስ ነፃነትን የሚያፍኑ ጥቃቶችን እና ማስፈራሪያዎችን እንዲያቆሙ አሳስቦ ነበር።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG