በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቡርኪና ፋሶ ቪኦኤን እና ቢቢሲን ለጊዜው አገደች


ፎቶ የግድግዳ ምስል በኡጋድጉ፣ ቡርኪና ፋሶ እአአ መጋቢት 1/2023
ፎቶ የግድግዳ ምስል በኡጋድጉ፣ ቡርኪና ፋሶ እአአ መጋቢት 1/2023

· ቪኦኤ እርምጃውን አውግዟል

ቡርኪና ፋሶ የቪኦኤን እና የቢቢሲ ስርጭቶችን ለጊዜው አግዳለች፡፡ እርምጃው የመጣው የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ’ሂውማን ራይትስ ዋች’ “የቡርኪና ፋሶ ሠራዊት በሲቪሎች ላይ በደል ይፈፅማል” ሲል ሪፖርት ማውጣቱንና ሁለቱ የሚዲያ ተቋማትም ይህንኑ በዜና በማሠራጫታቸው ነው።

‘የኮምዩኒኬሽን ከፍተኛ ም/ቤት’ የተሰኘው አካል ሁለቱ ዓላም አቀፍ የራዲዮ ጣቢያዎች ለሁለት ሣምንታት ፕሮግራሞቻቸውን እንዳያሰራጩ ትላንት ሐሙስ ትዕዛዝ አስተላልፏል። የቪኦኤ፣ የቢቢሲ እና የ’ሂውማን ራይትስ ዋች’ ድህረ-ገፆችም በቡርኪና ፋሶ ተደራሽ እንዳይሆኑ ተደርጓል።

ቡርኪና ፋሶን በተመለከተ የቀረበው ዘገባ ትክክለኛ እንደሆነ እንደሚያምን እና በዛች ሀገር ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ዘገባዎቹን በምልአትና በትክክለኛ መንገድ መሥራቱን እንደሚቀጥል ቪኦኤ አስታውቋል።

’ሂውማን ራይትስ ዋች’ የቡርኪና ፋሶ ሠራዊት በሲቪሎች ላይ በደል ይፈፅማል በሚል ያወጣውን ሪፖርት ተንተርሶ ቪኦኤ ባቀረበው ዘገባ፣ የቡርኪና ፋሶ ባለሥልጣናትን ምላሽ ለማካተት ሞክሮ እንዳልተሳካለት ታውቋል።

በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ያለችው ቡርኪና ፋሶ፣ ፍራንስ 24ን ጨምሮ፣ አምስት የሚሆኑ የፈረንሣይ ዜና ማሠራጫዎችን እና ጋዜጦችን ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ አግዳለች።

የአሜሪካ ድምፅ በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ የቡርኪና ፋሶ መንግሥት በትላንትናው ዕለት የጣቢያውን ፕሮግራሞች እና በኢንተርኔት የሚያቀርባቸውን ሌሎች የሚዲያ ውጤቶች ለሁለት ሣምንት ማገዱን አውግዟል።

ጣቢያው በተጨማሪም፣ ‘የኮምዩኒኬሽን ከፍተኛ ም/ቤት’ የተሰኘው አካል የሃገሪቱ ሠራዊት በሲቪሎች ላይ ይፈጽማል ከሚባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋራ የተገናኙ ዘገባዎችን ቪኦኤ እንዳይሠራ ማገዱን አውግዟል። ይፈፀማሉ ከሚባሉት የመብት ጥሰቶች ጋራ በተያያዘ የወጡ ሪፖርቶች፣ የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ እንዲረዱ ጥሪ እንዲቀርብ ማገዛቸውን የቪኦኤ መግለጫ አመልክቷል።

“ቡርኪና ፋሶን በተመለከተ የቀረበው ዘገባ ትክክለኛ እንደሆነ ቪኦኤ ያምናል፣ በዛች ሀገር ያሉትን ክስተቶች በተመለከተ ዘገባዎቹን በምልአትና በትክክለኛ መንገድ መሥራቱን ይቀጥላል” ሲሉ የቪኦኤ ተጠባባቂ ዲሬክተር ጃን ሊፕማን መናገራቸውን መግለጫው ጠቅሷል።

“ቪኦኤ ትክክለኛ፣ የማያዳላ፣ እና ሁሉን የሚያካትት የጋዜጠኝነት አሠራር መርሆችን በሚገባ እየተከተለ የሚሠራ በመሆኑ፣ የቡርኪና ፋሶ መንግሥት አሳሳቢ የሆነውን ውሳኔ እንደገና እንዲያጤነው እንጠይቃለን” ሲሉም አክለዋል ሊፕማን።

“ዓለም የፕሬስ ቀንን ልክ የዛሬ ሳምንት ለማክበር በሚዘጋጅበት ወቅት፣ መረጃን በነፃነት እንዳይንሸራሸር የሚገድብ እርምጃ መወሰዱ፣ ‘ነጻ ፕሬስ ሥፍራ አለው’ የሚለውን የቪኦኤ መሪ ቃል እውነተኛነት የሚያሳይ ተጨማሪ ምሳሌ ነው” ብለዋል ሊፕማን።

ለትርፍ ያልተቋቋመው ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ‘ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ’ እንደሚለው፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቡርኪና ፋሶ የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ በአፍሪካ ካሉ ተስፋ ከሚጣልባቸው ሃገሮች አንዷ ነበረች። ነገር ግን ከሁለት ዓመታት በፊት፣ በእ.አ.አ በጥር እና በመስከረም 2022 በተከታታይ የተፈጸሙትን መፈንቅለ መንግሥታት ተከትሎ የተከሰቱት ሁከቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በመረጃ ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አድርገዋል። በነጻ ፕሬስ የደረጃ ዝርዝርም ቡርኪና ፋሶ ከ180 ሃገራት 58ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG