በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቀድሞ የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚዳንት በቶማስ ሳንካራ ግድያ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው


ፎቶ ፋይል፦ ብሌዝ ኮምፓኦሬ እአአ ሰኔ 29/2011
ፎቶ ፋይል፦ ብሌዝ ኮምፓኦሬ እአአ ሰኔ 29/2011

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮማፓኦሬ እአአ በ1987 ከሳቸው በፊት በነበሩት ፕሬዚዳንት በቶማስ ሳንካራ ላይ በተፈጸመው ግድያ የተሰጣቸው የዕድሜ ይፍታህ እስራት ቅጣት ብዙዎች በቅርብ ዓመታት በብጥብጥ በሚታመሰው በዚያ የአፍሪካ አካባቢ የድል ዜና አድርገው አይተውታል።

ሳንካራ ከተገደሉ ከሠላሳ አራት ዓመታት በኋላ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኮምፓኦሬ እና የሌሎቹ አብረዋቸው የተከሰሱ አስራ አራት ሰዎች የክስ ሄደት የተከፈተው ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር። ከአስራ አራቱ ውስጥ ሦስቱ ከወንጀሉ ነጻ የተባሉ ሲሆን የተቀሩት ከሦስት ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ተወስኖባቸዋል።

ስድስት ወር በወሰደው የፍርድ ሂደት በመቶዎች የተቆጠሩ ምስክሮች ሳንካራን እና የእርሳቸውን ሰዎች ለመግደል ሴራ ሲጠነሰስ ነበር በማለት መስክረዋል።

የአፍሪካ ሀገሮችን በቅኝ ግዛትነት ይዘው የነበሩ ኃይሎችን በመቃወም አዘውትረው ይናገሩ የነበሩት ቶማስ ሳንካራ ፓን የአፍሪካውያን አንድነትን የሚያቀነቅኑ አብዮተኛ ተደርገው ይታያሉ።

እርሳቸው እና ሌሎችም ብዛት ያላቸው ሰዎች ዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ ውስጥ አአ በ1987 ጥቅምት ወር በብሄራዊ አብዮታዊ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ በጥይት መገደላቸው ይታወሳል። ሳንካራ እንዲገደሉ ሴራውን በማቀናበር ሲጠረጠሩ የቆዩት የቅርብ ጓደኛቸው የነበሩት ኮምፓኦሬ አስተባብለዋል። የቶማስ ሳንካራ ቤተሰብ ጠበቃ ቤኔዌንዴ ስታኒስላስ ሳንካራ የዕድሜ ልክ ቅጣት ውሳኔውን ተከትሎ በሰጡት ቃል፣

የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ እፎይታ ሰጥቶናል። ከዚያም በላይ ለቦርኪና ዳግም ትንሳኤ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ለአፍሪካ ትንሳኤም እንዲሁ የማይነካ ሰው እንደሌለ ሁሉም በስራው እንደሚጠየቅ በህግ ፊት ሁሉም እኩል መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ከሳንካራ መገደል በኅላ ስልጣን የያዙት ኮምፓኦሬ የቶማስ ሳንካራ ግድያ ጉዳይ እንዳይነሳ አፍነው ይዘው ለሃያ ሰባት ዓመታት ሀገሪቱን በአምባገነንነት ገዝተዋል። እአአ በ2014 ከሥልጣናቸው ከተገለበጡ በኅላ ወደ አይቮሪኮስት የተሰደዱት የፍርድ ሄደታቸው የተካሄደው በሌሉበት ነው።

XS
SM
MD
LG