በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያ እጅ በቡርኪና ፋሶው መፈንቅለ መንግሥት


በቡርኪና ፋሶው ያለፈው ሳምንት መፈንቅለ መንግሥት ወቅት በርካታ ሲቪሎችና የሰራዊት አባላት የሩሲያን ሰንደቅ ዓላማ በአደባባይ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።
በቡርኪና ፋሶው ያለፈው ሳምንት መፈንቅለ መንግሥት ወቅት በርካታ ሲቪሎችና የሰራዊት አባላት የሩሲያን ሰንደቅ ዓላማ በአደባባይ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

በቡርኪና ፋሶው ያለፈው ሳምንት መፈንቅለ መንግሥት ወቅት በርካታ ሲቪሎችና የሰራዊት አባላት የሩሲያን ሰንደቅ ዓላማ በአደባባይ ሲያውለበልቡ መታየታቸው ለምን ይሆን? ሲል የቪኦኤው ሄንሪ ዊልኪንስ ባደርገው ማጣራት፣ የሩሲያ የሃሰት መረጃ ሥርጭት በዚህኛው የቡርኪና ፋሶ መፈንቅለ መንግሥት ሚና እንደነበረው ማወቅ ተችሏል።

ዊልኪንስ ከዋጋዱጉ በላከው ዘገባ መሰረት፣ ባለፈው እሁድ አዲሱ የቡርኪና ፋሶ ሁንታ መሪ ኢብራሂም ትራኦሬ የቀድሞው ሁንታ መሪና ጊዜያዊ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ፖል ሄንሪ ዳሚባን ባስወገዱ በሁለተኛው ቀን፣ አንዱ ወታደራቸው ከአንድ የተሰረቀ የተመድ ወታደራዊ ተሽከርካሪ ውስጥ የሩሲያን ባንዲራ ይዞ ብቅ ብሏል።

በወቅቱ ውጥንቅጧ በወጣው ዋጋዱጉ በሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ የተሰባሰቡ ተቃዋሚ ሰልፈኞችም፣ የሩሲያን ባንዲራ አውለብልበዋል። የፈረንሳይን አጋርነት በሩሲያ መተካት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ኮንስታንቲን ጉየቭ የተባሉና በኔዘርላንድ መቀመጫውን ያደረገ የጥናት ተቋም ተመራማሪ እንዳሉት፣ በጎረቤት ማሊ በነበረው መፈንቅለ መንግሥት ሩሲያን የሚደግፉ የሚዲያ ውጤቶች ሁንታው የሽግግር ዕድሜውን ለማራዘም መወሰኑን ባሳወቀበት ወቅት ተሰራጭተው ነበር። በኋላም ዋግነር ግሩፕ የተሰኘው የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ወደ ሃገሪቱ እንዲጋበዝ የሚወተውቱ የሚዲያ ውጤቶች ተሰራጭተዋል።

አጨቃጫቂውን ዋግነር ግሩፕ የመሰረቱት የቭጌኒ ፕሪጎዚን ለአዲሱ ሁንታ መሪ ኢብራሂም ትራኦሬ በይፋ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ኤኤፍፒ እንደዘገበው፣ ትራኦሬና ሰዎቻቸው “አስፈላጊውን ነገር ለህዝባቸው ፈጽመዋል” ሲሉ የዋግነር ግሩፕ መስራቹ ተናግረዋል።

ፈረንሳይ ቡርኪና ፋሶ ለሰባት ዓመታት ከኢስላሚክ ስቴትና አል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ካላቸው አክራሪ የእስልምና ኃይሎች ጋር ለነበረባት ፍልሚያ አጋር ነበረች። አሁን ግን ሩስያውያኑ በተሻለ የቡርኪና ፋሶን ችግር ይቀርፋሉ የሚል አስተሳሰብ እያየለ መጥቷል።

“ለአሁኑ የተወሰነና ጊዜያዊ ጠቃሚ ውጤት ቢኖረውም፣ ለወደፊቱና ለዘለቄታው ግን ሩሲያ የቡርኪና ፋሶን ጸጥታ በተመለከተ ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል” ሲሉ ተንታኞች ተናግረዋል ሲል ሄንሪ ዊልኪንስ ሪፖርቱን አጠቃሏል።

XS
SM
MD
LG