በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቡርኬናቤ መንደር ሰባ ሰው ተጨፍጭፏል


ሰሜናዊ ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ሸማቂዎች ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ አድርሰውታል የተባለን ጭፍጨፋ እየመሩመሩ መሆናቸውን የሃገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

በአንዲት መንደር ውስጥ ተፈፀመ የተባለው መደዳ ግድያ ሰለባዎች በአብዛኛው ሕፃናትና አዛውንት መሆናቸው ተገልጿል።

በጭፍጨፋው የተገደለው ሰው ቁጥር ሰባ መድረሱን ባለሥልጣናቱ ትናንት፤ ሰኞ ቢያስታውቁም የአውሮፓ ኅብረት ግን መቶ እንደሚሆን ከትናንት በስተያ ጠቁሞ ነበር።

በአሥሮች የሚቆጠሩ ቤቶች እንደተቃጠሉበት የተነገረው ጥቃት የተፈፀመው ዛኦንጎ በምትባል መንደር ውስጥ መሆኑን የተናገሩት አቃቤ ሕግ ሲሞን ጋኑ ተጠያቂው ማን እንደሆነ እስካሁን እንደማያውቁ ገልፀዋል።

ህግ አስከባሪዎች ሁለት ቀን ሙሉ ስለ ጥቃቱ ሌሎችን ሳያነቁ መቆየታቸውንና መርማሪዎቹ አደጋው ቦታ የደረሱት ከአራት ቀናት በኋላ መሆኑን ጋኑ አመልክተው ቡድኑ ጉዞ ላይ ሳለ ጥቃት ተሰንዝሮበት እንደነበረ ተናግረዋል።

ከአል ቃይዳና ከአይሲስ ጋር ቁርኝት ካላቸው እሥላማዊ ፅንፈኞች ጋር ለዓመታት እየተፋለመች ያለችው ቡርኪና ፋሶ በግጭቶቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉባት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰው ተፈናቅሏል።

ጂሃዳዊ ጥቃቶቹ የዛሬ ዓመት መስከረም ውስጥ ሥልጣን በኃይል የያዘውን የአሁኑን ጁንታ ጨምሮ በሃገሪቱ ላይ የሁለት መፈንቅለ መንግሥት ሰበብ ሆነዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG