በኦሮሚያ ክልል ቡራዩ ከተማ፣ በእስር ላይ እንደሚገኙና ለአንድ ወር ያህል ማንም ጎብኚ እንዳላያቸው ሲነገር የቆየው፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራር አባላት፣ ማምሻውን ወደ ቡራዩ ፖሊስ መምሪያ መመለሳቸውን ጠበቃቸው አስታወቁ። ፓርቲው፥ እስረኞቹ ያሉበት ኹኔታ እንደሚያሳስበው ገልጿል።
ለአራት ዓመታት ያህል በእስር ላይ የሚገኙት የኦነግ አመራሮች ጠበቃ አቶ ቱሊ ባይሳ፣ ታሳሪዎቹ፣ በመጀመሪያ፣ ቡራዩ ፖሊስ መምሪያ ታስረው እንደነበር፣ በኋላም ለአንድ ወር ያህል የት እንደነበሩ ሳይታወቁ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ጠበቃው ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ ያለፈውን አንድ ወር በዱከም ፖሊስ መምሪያ በእስር ያለፉት አመራሮቹ፣ አኹን ደግሞ ወደ ቡራዩ ፖሊስ መምሪያ መመለሳቸውን ገልጸዋል። እስረኞቹ ለምን ከአንዱ ፖሊስ መምሪያ ወደ ሌላው እንደሚዛወሩ፣ የተነገራቸው ምክንያት አለመኖሩን፣ ጠበቃው አክለው ተናግረዋል።
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ለሚ ገመቹ፣ እስረኞቹ ያሉበት ኹኔታ አሳሳቢ እንደኾነ አመልክተዋል። ቃል አቀባዩ አያይዘውም፣ ስለ እስረኞቹ ኹኔታ፣ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ለተባሉ ተቋማት ኹሉ አቤቱታ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌዴራል መንግሥት ቃል አቀባዮች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ይኹንና ከዚኽ ቀደም፣ የአሜሪካ ድምፅ የጠየቃቸው፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ፣ “የታሰረ የኦነግ አመራር የለም፤” ሲሉ፣ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ቀደም ሲል አውጥቶት በነበረው መግለጫ፣ “ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራር አባላት በአፋጣኝ እንዲፈቱ፣ አልያም ያሰራቸው አካል ሕጋዊ ሒደቱን ተከትሎ፣ የክሥ መዝገብ ከፍቶ በአግባቡ እንዲጠይቃቸው አሳስቦ እንደነበር ይታወሳል።