በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ውስጥ ሦስት ፎቅ ያለው የመኖሪያ ሕንፃ ተደርምሶ ዐሥር ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ስምንት ሰዎች ቆስለዋል። ቁጥራቸው ለጊዜው ያለተለዩ ሰዎች ደግሞ በፍርስራሽ ውስጥ ጠፍተዋል ተብሎ እንደሚገመት የሀገሪቱ የመንግሥት ብዙኅን መገናኛ ዘግበዋል።
በካይሮ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኘውና ከርዳሳ በተባለው አብዛኛው የሠራተኛ መደብ በሚኖርበት አካባቢ ከተደረመሰው የሕንፃው ፍርስራሽ ውስጥ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት የሲቪል መከላከያ ቡድኖች ፍለጋ ላይ መኾናቸውን እና አምቡላንሶች ወደ ሥፍራው መላካቸውን አል-አክባር- አል -ዮም ጋዜጣ ዘግቧል።
ለሕንፃው መደርመስ “የጋዝ ሲሊንደር ፍንዳታ” ምክኒያት መኾኑን የዐይን እማኞቹን መናገራቸውን የጠቀሰው በመንግሥት የሚተዳደረው ብዙኅን መገናኛ ፣ ፖሊስ ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ዘግቧል።
የጊዛ ግዛት አዴል አል ናጋር ፣ ከአደጋው የተረፉት ለደኅንነታቸው ሲባል ሕንፃውን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ እና አቅራቢያ ወደሚገኙ ሕንፃዎች እንዲዛወሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን የግዛቲቱ አስተዳደር በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።
ከ26 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት በካይሮ ከተማ እየተስፋፋ በመጣው በመጣው የግንባታ ሥራዎች፣ የግንባታ ሕግና ደንቦች እምብዛም አይተገበሩም።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማዋ የሕንፃዎች መደርመስ እየተበራከተ መጥቷል። ይኽም በግንባታ ወቅት በሚፈጠሩ ቸልተኝነትና የግንባታ ሕጎችን ባለማክበር ነው።
መድረክ / ፎረም