የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ጋራ ባደረጉት ውይይት፤ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም፣ ኪቭን ያሳተፈ እና በአውሮፓ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች የሚደገፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ መወሰናቸውን አስታወቁ።
ትላንት ሐሙስ በዋይት ሐውስ ያካሄዱትን ስብሰባ ተከትሎ ስታርመር በሰጡት መግለጫ እቅዱ "ዩክሬን ተግባራዊ የምታደርገው እና ፑቲን እንዳይመለስ በሚያስችል ኅይል የሚደገፍ ጠንካራ እና ፍትሃዊ የሆነ ሰላም ማምጣት" መሆኑን ተናግረዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ሰኞ ዕለት ከትራምፕ ጋራ በዋይት ሐውስ በነበራቸው ውይይት፣ “አጥቂውን የሚሸልም ስምምነት ሰላም ሊያመጣ አይችልም” ሲሉ ከተናገሩት ጋራ የሚመሳሰል አስተያየት የሰጡት ስታርመር፣ አጥቂዋ ደግሞ ሩሲያ መሆኗን አፅንዖት ሰጥተው አመልክተዋል።
ስታርመር አክለው ከሌሎች የአውሮፓ መሪዎች ጋራ በቅርበት ለመሥራት ቃል የገቡ ሲኾን፣ እንግሊዝ ከአጋሮቿ ጋራ በመኾን የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ለማሰማራት ዝግጁ መኾኗንም አስታውቀዋል።
ትራምፕ በበሉላቸው፣ ስታርትመር እንደቅድመ ሁኔታ ያስቀመጡትን፣ ዩናይትድ ስቴትስ የአውሮፓ ሰላም አስከባሪ ኅይሎችን የመደገፍ ሚና ጨምሮ፣ ምንም ዐይነት የፀጥታ ዋስትና ለመስጠት ቃል ከመግባት ተቆጥበዋል።
"ስምምነት ላይ እስከምንደርስ ድረስ ስለሰላም ማስከበር ማውራት ደስ አይለኝም" ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተናገሩት ትራምፕ "የመጥፎ ዕድል ምልክት ማሳየት አልፈልግም" ብለዋል።
ትራምፕ በንግግራቸው የደኅንነት ድጋፉን የሚሰጡት፣ አሜሪካ የዩክሬንን ልዩ ማዕድናት ማግኘት የሚያስችላት እና የጆ ባይደን አስተዳደር የሀገሪቱን ጦርንት ለመደገፍ ያወጡትን ገንዘብ እንደሚያስመልሱ የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ ከደረሱ ብቻ ሊሆን እነደሚችል ጠቁመዋል።
መድረክ / ፎረም