በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእንግሊዝን የመውጣት ጉዳይ ፓርላማው ወሰደ


የእንግሊዝን ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትሯ እጅ ለማውጣትና እራሳቸው ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን ድምፅ የሃገሪቱ እንደራሴዎች ትናንት ምሽት ላይ ሰጥተዋል።

ሕግ አውጭዎቹ በእንግሊዝም በአውሮፓ ኅብረትም ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል የመደራደሪያ ሰነድ ለማዘጋጀት ነው እያሰቡ ያሉት።

በተከታታይ በከሸፉትና በተጨናገፉት የእንግሊዝና የአውሮፓ ኅብረት ድርድሮች የተሰላቹ የሚመስሉት የፓርላማው የሕግ መምሪያ አባላት 329 ለ302 በሆነ ድምፅ ነው የሃገራቸውን ከኅብረቱ የመውጣቱ ኃላፊነት ለመቆጣጠር የወሰኑት።

ለውሣኔው ማለፍ የሦስት የሜይ ካቢኔ ሚኒስትሮች በፈቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቅ እገዛ እንዳደረገም ነው የማሰማው።

ይህ ውሣኔ ሕግ አውጭዎቹ ሁሉም ወገኖች ሊስማሙባቸው ይችላሉ የሚባሉ የመደራደሪያ ሃሣብ አማራጮችን ለመፈተሽ ዕድል እንደሚሰጣቸው ተነግሯል።

የእንደራሴዎቹ እንዲያ ዓይነት ውሣኔ ማሳለፍ ፓርላማው ያለበትን መንግሥቱን ተጠያቂ የማድረግ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል የሌበር ፓርቲው መሪ ጀረማይ ኮርቢን።

“ሁለት ጊዜ የወደቀ የመደራደሪያ ሃሣብ ይዞ ለመቅረብ የሚያስችል መንገድ ለመፈለግ ከመጣር ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ወደ ፍጥጫና ንትርክ የማይወስድ ዕቅድ እንዲኖረን የሚያስችል ድምፅ እንዲገኝ የሚያስችል ሁኔታን ቢያመቻቹ ነበር የሚሻለው። ድምፅ የማያገኝ ሃሣብ ይዘው መቅረብ፤ በተመሣሣይ ጊዜ ደግሞ ድምፅ ሊያገኝ የሚችልን ሃሣብ የሚያደናቅፍ አቋም ሊይዙ አይችሉም” ብለዋል።

ፓርላማው የሃገሪቱን ከአውሮፓ ኅብረት የመውጣት ጉዳይ እራሱ ሊመራው መወሰኑ “የዴሞክራሲ ተቋማቱን የመቆጣጠር እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድበት አይገባም” ባይ ናቸው ኮርቢን በፓርላማው መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ግን የእንግሊዝ ሕዝብ የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ በድምፁ ባሳለፈው ውሣኔው መሠረት ሃገሪቱ የፊታችን ዓርብ፤ መጋቢት 19 ለንደን ላይ ዕኩለ ሌሊት ሲሆን ከኅብረቱ መሰናበቷን ለማረጋገጥ የሚያስችል ደረጃ ላይ ለመድረስ ፓርላማው ባለፈው ሣምንት ባሳለፈው ውሣኔ ብቻ መገዛት ይኖርብናል ብለዋል ለእንደራሴዎቹ ሲናገሩ።

“እርግጥ ነው፤ የተከበሩ እንደራሴ እንዳሉት አሁን ነገሮች ባሉበት ሁኔታ ትርጉም ያለው ድጋፍ የሚያስገኝ የድርድር ሃሣብ ይዞ ለመመለስ ይቻላል የሚል ዕምነት እንደሌለኝ ተናግሬአለሁ። በተጨማሪም ግን የእንግሊዝን ከኅብረቱ መሰናበት ለማረጋገጥ የሚያስችል ድምፅ በዚህ ምክር ቤት ውስጥ ለማግኘት ተስፋ ያደረግኩበትን ሃሣብ ይዤ ለመመለስ በፓርላማው ውስጥ ካሉ ባልደረቦቼ ጋር እየመከርኩ መሆኔንም ጠቁሜአለሁ” ብለዋል ሜይ።

ይሁን እንጂ በሃገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማሳረፍ አቅም ባለው ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የመፋታት ውስብስብ ጉዳይ ላይ ሃሣባቸውንና የቀደመም ውሣኔያቸውን የመከለስ አዝማሚያ አሁን ከእንደራሴዎቹ ብዙዎችና ከእንግሊዛዊያንም እየታየ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት ለሜይ መንግሥት ተጨማሪ ዕድሜ ለመስጠት ወስኗል። እስከ ፊታችን ሚያዝያ አራት ትርጉም ያለው ሃሣብ ይዘው ቢመለሱ ተቃውሞ የለውም።

ለንደን እንግዲህ አንድም ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በሰላም እየተናገደች የምትቀጥልበትን ምቹና ለጉዳት የማያጋልጥ ሃሣብ ይዛ መምጣት አለባት፤ አለበለዚያም ይህንን ብሬግዚት የሚሉ የፍቺ ሃሣቧን እርግፍ አድርጋ ጥላ በኖረችበት የሞቀ ቤቷ፤ በአባልነቷ መቀጠል ይኖርባታል።

ለተጨማሪ ዘገባ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የእንግሊዝን የመውጣት ጉዳይ ፓርላማው ወሰደ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:42 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG