በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እንግሊዛዊው የኦሊምፒያን ሞ ፋራህ ዕውነተኛ ማንነቱን ገለፀ


እንግሊዛዊው አትሌት ሞ ፋራህ
እንግሊዛዊው አትሌት ሞ ፋራህ

ከኦሊምፒክ አደባባይ አራት የወርቅ ሜዳልያዎች ያሸነፈውና በንግሥቲቱ የ“ሰር”ነት ማዕረግ የተሰጠው እንግሊዛዊው ገናና አትሌት ሞ ፋራህ በልጅነቱ በህገ ወጥ መንገድ በሌላ ልጅ ስም ወደእንግሊዝ መወሰዱንና በቤት ሠራተኝነት እንዲያገለግል መደረጉን ተናገረ።

የሠላሳ ዘጠኝ ዐመቱ ሞ ፋራህ ለቢቢሲ በሰጠው ቃል “ሞ ፋራህ” የሚለውን ስም የሰጠችው የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ በህገ ወጥ መንገድ ከጅቡቲ ወደ እንግሊዝ የወሰደችው ሴት መሆኗን ገልጿል።

የአራት ዓመት ህፃን ሳለ ወላጅ አባቱ ሶማሊያ ውስጥ በነበረው የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንደተገደሉበት የተናገረው ሞ ፋራህ ዕውነተኛ ስሙ “ሁሴን አብዲ ካሂን” መሆኑን ገልፆ ወደ እንግሊዝ ከተወሰደ በኋላ የሌላ ቤተሰብ ልጆች በመጠበቅ እንዲያገለግል ተደርጎ እንደነበር ተናግሯል።

ሞ ፋራህ ነገ ረቡዕ በሚቀርበው ዘጋቢ ፊልም ላይ የተወለደው ሰሜናዊ ሶማሊያ ሶማሊላንድ ውስጥ መሆኑን፤ አባቱን በጦርነቱ ካጣ በኋላ ቤተሰቡ መበተኑን፤ ወላጆቹ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ኖረው እንደማያውቁና ቀደም ሲል ይናገር የነበረው እውነት አለመሆኑን፤ ወደ እንግሊዝ እንዲገባ የተድረገው ከወላጅ እናቱ ተነጥሎ መሆኑን ይተርካል።

በረጅም ርቀት ሩጫ አራት የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ የመጀመሪያ እንግሊዛዊ የሆነው ሞ ፋራህ ዕውነተኛ ታሪኩን እንዲናገር ያበረታቱት ልጆቹ መሆናቸውን ገልጿል።

ወንድ ልጁን ሁሴን ብሎ በራሱ ዕውነተኛ ስም የሰየመው ሞ ፋራህ "ስሙን ወስጄ አውሮፕላን ላይ ወጥቼ የሄድኩበትን የውነቱን ሞ ፋራህን ብዙ ጊዜ አስበዋለሁ። ደህና እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል።

XS
SM
MD
LG