ደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ ውስጥ ላለፉት ስምንት ቀናት ሲደራደሩ የቆዩት የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውን የአፍሪካ ኅብረት ዋና አደራዳሪ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ አስታወቁ።
ሥምምነት ላይ ከተደረሰባቸው ነጥቦች መካከል በሥርዓት የሚመራና በተከታታይ የሚካሄድ ትጥቅ መፍታት፣ የአገልግሎቶች ቅንጅት፣ የሲቪሎች፣ የሴቶች፣ ህፃናትና አረጋዊያን ጥበቃ፣ በሃገር ውስጥም በውጭም ላሉ ሁሉ ጥበታ ማድረግ እንደሚገኝባቸው ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ አስታውቀዋል።
የሥምምነቱን አፈፃፀም የአፍሪካ ኅብረት ቡድን እንደሚከታተል ኦባሳንጆ አስታውቀዋል።
ከኦባሳንጆ ቀጥለው የተናገሩት የኢትዮጵያ መንግሥት ቡድን መሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና የህወሓት ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የአፍሪካ ኅብረት ስላደረገው ጥረት አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሥምምነቱ ተግባራዊነት ተግቶ እንደሚሠራ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲጠናከር፣ ብሄራዊ ውይይት እንዲካሄድ እንደሚሠራ አምባሣደር ሬድዋን አስታውቀዋል።
“ተጫነብን” ባሉት ጦርነት በመቶ ሺሆች የክልሉ ተወላጆች መገደላቸውን፣ ህፃናት እንደማይማሩ፣ ሆስፒታሎች አገልግሎት እንደማይሰጡ የተናገሩት አቶ ጌታቸው ሥምምነቱን የፈረሙት ለትግራይም በጠቅላላውም የኢትዮጵያ ህዝብ ለሠላም ዕድል ለመስጠት እንደሆነ አመልክተዋል።
ሥምምነቱ ፈጥኖ ተግባራዊ እንዲሆን የጠየቁት አቶ ጌታቸው የእርሳቸው ወገን የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ሁለቱም የቡድኖቹ መሪዎች ነገ ሁለት ዓመቱን የሚደፍነው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሃገሪቱ ውስጥ ስላደረሰ ጥፋት ተናግረዋል።