በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቀድሞ የብራዚል ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ሆስፒታል ገባ


የቀድሞ ኮከብ የብራዚል እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ
የቀድሞ ኮከብ የብራዚል እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ

የቀድሞ ኮከብ የብራዚል እግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ለካንሰር ህክምና ሆስፒታል መግባቱን ሴት ልጁ ኬሊ ናሲሜንቶ ትናንት ረቡዕ በማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ አስታውቃለች።

ይሁን እንጂ ለህይወት የሚያሰጋው ያልተጠበቀ አስቸኳይ ችግር ያልገጠመው መሆኑንም ናሲሚንቶ አክላ ማስታወቋን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

ናሲሜንቶ ኢንስታግራም ላይ ያሰፈረችው ጽሁፍ የወጣው ኢኤስፒኤን ብራዚል ፔሌ የሰውነቱ ክፍሉ ላይ እብጠት ስለገጠመው አልበርት አንስታይን ሆስፒታል ገብቶ ብዙ የጤና ምርመራዎች እየተካሄዱለት የሚል ዘገባ ካወጣ በኋላ መሆኑ ተዘግቧል።

ናሲሜንቶ በጽሁፏ “የአባቴን ጤንነት አስመልክቶ ዛሬ በመገናኛ ብዙሃን በርካታ አስደንጋጭ ዜናዎች ወጥተዋል እሱ ሆስፒታል ውስጥ ሆኖ የህክምና ክትትል እየተደረገለት ነው። ድንገተኛ ወይም አዲስ የሆነ ነገር የለም። ለአዲስ ዓመት ከሱ ጋር ሆኜ አዳዲስ ፎቶግራፎችን እንደማወጣ ቃል እገባለሁ” ብላለች።

የ82 ዓመቱ ፔሌ ባለፈው መስከረም 2014 ዓም በአንጀት ካንሰር ህክምና ትልቅ እጢ ከተወገደለት በኋላ በቋሚነት ሆስፒታል እየተመላለሰ ህክምናውን ሲወስድ እንደነበር ተመልክቷል።

ኢኤስፒኤን ብራዚል ባወጣው ዘገባ ፔሌ የልብ ችግር እየገጠመው ሲሆን ሀኪሞች የኪሞቴራፒ ህክምናው የተጠበቀውን ውጤት እያመጣ አይደለም የሚል ስጋት እየገባቸው ነው ሲል ዘግቧል።

የፔሌ ሥራ አስኪያጅና የአልበርት አነስታይን ሆስፒታል ስለ ጉዳዩ ምንም አስተያየት አለመስጠታቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG