ዋሺንግተን ዲሲ —
ቦትስዋና በድንበሮቿ ላይ በምታካሂደው ጥብቅ የኮቪድ-19 ምርመራ የተነሳ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እንግልት ደርሶብናል ብለው እያማረሩ ናቸው። ቦትስዋና እስካሁን ያገኘቻቸው የተረጋገጡ የኮሮናቫይረስ ተያዦች ሠላሳ አምስት ሲሆኑ በበሽታው የሞተው አንድ ሰው ብቻ መሆኑ ተገልጿል። ይሁን እንጂ ቫይረሱ ከሌላ ሀገር ይገባል በሚል ስጋት የድንበር ኬላዎች ላይ ምርመራ ከጀመረች ቆይታለች።
የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ተመርምረን ለማለፍ እስከ አምስት ቀን ሊወስድብን ይችላል፤ የመኪናዎቹ ሰልፍ አስር ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከመሆኑ ባሻገር የመታጠቢያ አገልግሎት የለም የያዝነው ስንቅም እያለቀ እንቸገራለን ሲሉ አሽከርካሪዎቹ ተናግረዋል።