በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ በቦምብ ጥቃት በርካቶች ተገደሉ


በሶማሊያዋ የታችኛው ሸበሌ ግዛት የደረሱ ሁለት የቦምብ ጥቃቶች የግዛቲቱን ዋና ከተማ ከንቲባ ጨምሮ ለ18 ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ። እጅግ የከፋ መሆኑ ለተነገረው ጥቃት እስላማዊ ጽንፈኛ ቡድን አልሸባብ ኃላፊነት ወስዷል።

የመጀመሪያው በሶማሊያ የታችኛው ሸበሌ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው መርካ ከተማ ባለሥልጣናት ላይ የተነጣጠረ በአጥፍቶ ጠፊ የተሰነዘረ የቦምብ ጥቃት ነው። በጥቃቱም የከተማይቱ ከንቲባ አብዱላሂ አሊ ዋፎ እና ሌሎች 10 ሰዎች ሲገደሉ በርካታ የከንቲባው ጠባቂዎችም የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።

አንድ የግዛቲቱ የጸጥታ ጉዳዮች ባለሥልጣን ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት የቦምብ ጥቃቱ የተፈፀመው ከመርካ አስተዳደር ዋና መሥሪያ ቤት አቅራቢያ ነው።

ከፍንዳታው መጠን አንጻር የሟቾች ቁጥር ገና ሊጨምር እንደሚችል በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፍቃድ ስለሌላቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የግዛቲቱ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

መርካ ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በ92 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የወደብ ከተማ ናት።

በሌላ ያልተያያዘ ድንገት በዛሬው ዕለት አፍጎዬ ከተማ ውስጥ ከሚገኝ የተጨናነቀ የእንስሳት መሸጫ ሥፍራ የደረሰ የቦምብ ፍንዳታ፤ የዓይን እማኞች እና የህክምና ምንጮች ለአሜሪካ እንደተናገሩት፣ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 14 ሰዎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ፖሊስ እንዳመለከተው ፍንዳታው የደረሰው መሬት ውስጥ በተቀበረ ፈንጂ ነው።

አልሸባብ በበኩሉ በፍንዳታው ሁለት የኬንያ ወታደሮች መገደላቸውን ቢያመለክትም “ጥቃቱን የፈጸምኩት እኔ ነኝ” በሚል ግን ኃላፊነት አልወሰደም።

ሆኖም በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ከምትገኘው የማንዴራ ከተማ አቅራቢያ የኬንያ ወታደሮችን በጫነ ተሽከርካሪ ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን ተናግሯል።

በተያያዘ ዜና እስላማዊው ሸማቂ ቡድን ከቅርብ ቀናት ወዲህ የጥቃቱን መጠንና ስፋት እየጨመረ መምጣቱ ተዘግቧል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ገብተው ከኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት መፍጠራቸው ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG