ዋሽንግተን ዲሲ —
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በአምስት ክፍለ ግዛት የሚገኙ ስድስት ታሪካዊ የጥቁር ዩኒቨርስቲዎች ትናንት ሰኞ የቦምብ ፍንዳታ ማሰፈራሪያ የደረሳቸው መሆኑ ተሰምቷል፡፡
አብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎች ማስፈራሪያውን ተከትሎ ለተወሰነ ጊዜ ተዘግተው መቆየታቸውም ተነግሯል፡፡
ማስፈራሪያው የተላከላቸው ዩኒቨርስቲዎቹ ለተማሪዎቻቸው የማስጠንቀቂያ መልዕክት የላኩ ሲሆን የአደጋዎቹ ማስጠንቀቂያዎች የተሰነዘሩት በቀጥታ በመማሪያ ህንጻዎቹ ላይ እንደነበር ተመልክቷል፡፡
በጆርጅያ የአልባኒ ዩኒቨርስቲ፣ በዩኒቨርስቲ ህንጻዎች ላይ የቦምብ አደጋዎች ሊካሄዱ ይችላል የሚል ዛቻ እንደደረሰው በማሳሰብ ተማሪዎቹን በማኅበራዊ ሚዲያ ማስጠንቀቁ ተዘግቧል፡፡
የዛቻው ማስጠንቀቂያ ከደረሳቸው ታሪካዊ የጥቁር ዩኒቨርስቲዎች መካከል በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የሀዋርድ ዩኒቨርስቲ፣ የሜሪላንዱ ቡዊ ዩኒቨርስቲ፣ በሉዊዚያና የሚገኘው የኤምኤንድኤም ኮሌጅ፣ የፍሎሪዳው ቤተን ኩክማን ዩኒቨርስቲ እና የደለዌር ክፍለ ግዛት ዩኒቨርስቲ እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
ኤፍቢአይ ስለ ቦምብ ጥቃት ዛቻው የሚያውቅ መሆኑን ገልጾ፣ እንዲህ ያለውን ነገር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ለማስፈራሪያው ድርጊት እስካሁን ተጠያቂም ሆነ ተጠርጣሪ አካል ስለመኖሩ በአሶሼይትድ ፕሬስ ዘገባ አልተገልጸም፡፡