በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን አደጋ ምርመራ


ባለፈው መጋቢት የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን አደጋ ከመድረሱ በፊት፣ ተጨማሪ የግፊት ኃይል መስጫው በርቶ ወይም እየሰራ እንደነበር፣ አንድ የአሜሪካ ታዋቂ ጋዜጣ ዘገበ።

'The Wall Street Journal' የተሰኘው ጋዜጣ ዛሬ ዐርብ እንደዘገበው ከሆነ፣ በቅድመ ምርመራው ወቅት የነበሩ ምንጮቻቸው፣ ውጤቱ ሲገለጽ በሥፍራው ተገኝተው ገለፃ ተደርጎላቸዋል።

ከቦሌ ዓለማቀፍ ጣቢያ በተነሳ በ6 ደቂቃ ውስጥ ቢሾፍቱ አካባቢ በተከሰከሰው በዚያ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ፣ ስምንት የአውሮፕላኑ ሰራተኞችና 149 መንገደኞች በሙሉ መሞታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያው አደጋ፣ ባለፈው ጥቅምት ወር ኢንዶኔዥያ ውስጥ ተመሳሳዩ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን በተነሳ በጥቅት ደቂቃ ውስጥ ተከስክሶ ለ189 ሰዎች ሞት ምክንያት ከሆነው ጋር ተመሳሳይ መሆኑም ታውቋል።

በኢንዶኔዥያው ምርመራም ያነጣጠረው፣ እንደ ኢትዮጵያው ሁሉ፣ የአውሮፕላኑ ተጨማሪ የግፊት ኃይል መስጫ በርቶ ወይም እየሰራ እንደነበር ታውቋል።

የአውሮፕላኑ አምራች ቦይንግ ፋብሪካ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ገደማ እንዳስታወቀው፣ ቦይንግ 737 ላይ ያለውን ተጨማሪ የግፊት ኃይል መስጫ ሶፍትዌር ደረጃ ከፍ ለማድረግ የጀመረውን ሥራ፣ በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከወደቀው አውሮፕላን ጋር በተያያዘ፣ እዚህ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኝ አንድ የፌዴራል ፍርድ ቤት፣ ትናንት ሐሙስ ክስ መመስረቱም ታውቋል።

ኢሊኒዮስ ግዛት ውስጥ የተመሰረተው ይህ ክስ፣ ሕይወቱን በኢትዮጵያው አደጋ በአጣው የሩዋንዳ ዜጋ ጃክሰን ሙሶኒ ቤተሰብ ነው።

ቦይንግ፣ 737 ማክስ ኤይትን ሲፈበርክ፣ ተገቢውን ጥንቃቄ አላደረም ይላል ክሱ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ማክስ 8 ያላቸው አየር መንገዶች፣ ከአደጋው በኋላ አውሮፕላኑ እንዳይበር አድርጓል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG