በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር በሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ 85 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረ ቦይንግ 737 አውሮፕላን ከመሮጫ መንገዱ በመንሸራተቱ አስር ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የአገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሐሙስ እለት አስታወቁ።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ኤል ማሊክ ንዲአዬ እንደተናገሩት፣ በትራንስ ኤይር ስር የሚተዳደረው የሴኔጋል አየር መንገድ ረቡዕ እለት 79 መንገደኞችን፣ ሁለት አብራሪዎችን እና አራት የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ ወደ ባማኮ ሊጓዝ ነበር።
ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በሆስፒታል ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን፣ የቀሩት ለማረፍ ወደሆቴል ተወስደዋል።
ስለአደጋው ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ባይቻልም፣ የአየር መጓጓዣ ደህንነት የተሰኘ፣ በአየር መንገዶች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን የሚከታተል መረብ ቀድሞ ትዊተር ይባል በነበረው የኤክስ ማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ይፋ ያደረጋቸው ፎቶዎች፣ ሳር በበዛበት ሜዳ ውስጥ የገባው ጉዳት የደረሰበት አውሮፕላን በእሳት መከላከያ ፎም ተከቦ ያሳያል። በተጨማሪም ፎቶዎቹ አንደኛው የአውሮፕላኑ የሞተር ክፍል መሰበሩን እና ክንፉም መጎዳቱን ያሳያሉ።
መድረክ / ፎረም