በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሊንከን የአሜሪካ አጋሮች አይሲስን ድል የመምታት ትኩረታቸውን እንዲገፉበት አሳሰቡ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ

የዓለም አቀፉ ህብረት አጋሮች አይሲስን ድል የመምታት ትኩረታቸውን እንዲገፉበት የጠየቁት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ቡድኑ አፍሪካ ውስጥ ያሉትን ግብረ አበሮቹን መጋፈጥን የተለየ ትኩረት ሰጥተን መታገል ይኖርብናል ሲሉ አሳሰቡ።

አንተኒ ብሊንከን ጣሊያን ውስጥ "እስላማዊ መንግሥት ቡድን ድል መምታት" በተባለው ስብስብ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር "አንድ ላይ ሆነን በመስራታችን ትልቅ ውጤት ልናመጣ ችለናል። ይሄን አሸባሪ ቡድን በወሳኝነት ድል እስከምናደርገው ድረስ ትኩረታችንን እንድንቀጥል እጠይቃለሁ ብለዋል።

ህብረቱ ባደረጋቸው ጥረቶች ባዕዳን ተዋጊዎች ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ ረገድ ትልቅ እርምጃ አስመዝግቧል ሲሉም ተናግረዋል።

አስከትለውም የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሶሪያ ዲሞክራሲያዎ ኃይሎች አስር ሺህ የእስላማዊ መንግሥት ቡድን ታጣቂዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ገልፀው በዚህ ሁኔታ ሊቀጥል ስለማይችል መንግሥታት ተሃድሶ ለመስጠት ወይም ህግ ፊት ለማቅረብ ዜጎቻቸውን እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

አስከትለውም ሚኒስትር ብሊንከን ለሶሪያውያን እና በአካባቢው ላሉ ሶሪያውያን ስደተኞችን ላስጠለሉ ማኅበረሰቦች ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውል ተጨማሪ 436 ሚሊዮን ዶላር ሃገራቸው እንደምትሰጥ አስታውቀዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ እስላማዊ መንግሥት ቡድንን ለማሸነፍ ባቀናጀችው ህብረት በአሁኑ ወቅት ሰማኒያ ሦስት አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ። ዛሬም የሶሪያን ጦርነት ማቆም ስለሚቻልበት መንገድ በትለይ የሚያተኩር ጉባኤ ይካሄዳል።

ዛሬ ቀደም ብሎም የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቫቲካንን በመጎብኘት ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከሌሎችም ባለሥልጣናት ጋር የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሰብዓዊ መብት ከበሬታ እና ህገ ወጥ የሰው ዝውውርን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

XS
SM
MD
LG