በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሊንከን በብሪታንያ ጉብኝታቸው ፊታቸውን ወደ ዩክሬን መልሶ ማቋቋም መልሰዋል


የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ
የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ

የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ዩክሬን፥ በሩሲያ ወረራ ከደረሰባት ጉዳት እንድታገግም ለመርዳት ለተቀመጠው ግብ፣ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማስተባበር ከሚካሔደው ጉባኤ አስቀድሞ፣ ከብሪታኒያ እና ከዩክሬን አቻዎቻቸው ጋራ ተገናኝተው ለመነጋገር፣ በዛሬው ዕለት ወደ ለንደን አቅንተዋል።

ነገ ረቡዕ እና ከነገ በስቲያ ኀሙስ የሚካሔደውን ጉባኤ በጋራ የሚያስተናግዱት፣ ብሪታንያ እና ዩክሬን ናቸው። የዛሬው “የዓለም የስደተኞች ቀን” አካል በኾነ ኹነት፣ ብሊንከንና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ፣ ከጦርነቱ ሸሽተው የመጡ ዩክሬናውያን፣ ከእንግሊዝ አገር ሕይወት ጋራ ለመላመድ የሚያግዝ ምክር እና ድጋፍ ለመስጠት የተቋቋመውንና በለንደን ከተማ የሚገኘውን ማዕከል ጎብኝተዋል።

ብሊንከን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሌቨርሊ ጋራ፣ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ከዩክሬኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ጋራ ወደሚያደርጉት ሌላ ውይይት አምርተዋል።

በሌላ ዜና፣ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ፣ ዩክሬንን መልሶ ለማቋቋም ከታለመው ጉባኤ በፊት፣ ትላንት ሰኞ፣ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋራ በስልክ እንደተነጋገሩ ተዘግቧል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ “ለዩክሬን፥ ጠንካራ የመንግሥታት እና የግሉን ዘርፍ ድጋፍ ለማጉላት እና ቀጣይነት ያለውን የዩክሬንን ማሻሻያ ለማሳየት ልዩ ዕድል ነው፤” ብሏል።

ብሪታንያ፣ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በየካቲት 2022፣ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ፣ ለዩክሬን በምትሰጠው ወታደራዊ ርዳታ ግዙፍነት፣ ከዩናይትድ ስቴትስ በመቀጠል ሁለተኛዋ ሀገር ናት።

ዘሌንስኪ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፣ ጉባኤው ዩክሬንን መልሶ ለማቋቋም፣ በተለያየ መልኩ የሚደረጉትን ጥረቶች ያጠናክራል፤ ብለው እንደሚያስቡና “የተያዘው ጥረት፥ ነፃነት ፈጽሞ የማይበገር ዕሤት እንደኾነ ለዓለም ማሳየት አለበት፤” ብለዋል።

ዜለንስኪ፣ ዘወትር ምሽት፣ ለዩክሬን ሕዝብ በቴሌቭዥን የሚያሰሙት ዲስኩር አካል በኾነው የትላንት ምሽቱ ንግግራቸው፣ ብሪታንያ፥ እንዳይንቀሳቀስ ተይዞ የቆየውን የሩሲያ ገንዘብ፣ ለዩክሬን መልሶ ግንባታ እንዲውል የሚያስችል ዐዲስ ሕግ ማውጣቷን አመስግነዋል።

XS
SM
MD
LG