በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጠ/ሚ አብይ እና ብሊንከን በስልክ ተወያዩ


ፎቶ ፋይል፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ
ፎቶ ፋይል፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ሁኔታ አዲስ መግለጫ አውጥቷል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ትናንት በስልክ ማነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት አጭር መልዕክት በትግራይ ክልል የቀጠሉት ቀውሶች ዩናይትድ ስቴትስን እያሳሰቡ መሆናቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እንደገለፁላቸው ተናግረዋል።

ግጭቶቹ እንዲቆሙና የሲቪሎችን ደኅንነት ለመጠበቅ አስቸኳይ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እንዳሳሰቧቸውና ዩናይትድ ስቴትስ ግጭቶችን በመፍታት ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነች ያሳወቋቸው መሆኑንም ብሊንከን ገልፀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በመሥሪያ ቤቱ ዌብሳይት ላይ ባወጡት ፅሁፍ “ብሊንከን ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉት ሰብዓዊ ሁኔታና የሰብዓዊ መብቶች ቀውሶች ዩናይትድ ስቴትስን ማሳሰባቸውን አጠንክረው ገልፀውላቸዋል” ብለዋል።

ፕራይስ በመቀጠል በክልሉ ውስጥ ስለተፈፀሙ የጭካኔ አድራጎቶች፥ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና በደሎችን የሚያሳዩ ተዓማኒ ዘገባዎች ቁጥር እያደገ መሆኑን ብሊንከን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንሳታቸውንና የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኞችን ጨምሮ የሲቪሎችን ደኅንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ሁከቱ እንዳቀጥል ለመከላከል አስቸኳይና ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ ማሳሰባቸውን አመልክተዋል።

ኔድ ፕራይስ አክለውም “ግጭቱ ፈጥኖ እንዲቆም፣ የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎችና የኤርትራን ወታደሮችን ጨምሮ የውጭ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን አጥብቀው ጠይቀዋቸዋል” ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት “ተፈፅመዋል” ስለተባሉት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና በደሎች ነፃና ተዓማኒ ምርመራ ለማመቻቸት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እንዲሠራ፣ የድርጊቶቹን ፈፃሚዎች በተጠያቂነት እንዲይዝ ሚኒስትር ብሊንከን ማሳሰባቸውንም ፕራይስ አመልክተዋል።

ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ረድዔት ባልተገደበ ሁኔታ እንዲደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት መፍቀዱን እንደሚያውቁ አሜሪካዊው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለፃቸውንና የገባውን ቃል እንዲያከብር መጠየቃቸውን፣ ዩናይትድ ስቴትስም ለችግር ለተጋለጡ ኢትዮጵያዊያን ህይወት አድን ሰብዓዊ እርዳታ መለገሷን እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን ኔድ ፕራይስ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት “ትግራይ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ስላለው ሕግን የማስከበር ዘመቻ” በሚል ርዕስ ዛሬ ባወጣው ዝርዝር መግለጫ መንግሥቱ ክልሉ ውስጥ እያካሄደ ያለውን ዘመቻ አነሳስና የፌደራል መንግሥቱን ጣልቃ መግባት የገፋውን “ወንጀለኛ” ያለው የህወሃት ቡድን “ፈፅሟቸዋል” ያላቸውን “የሕገ መንግሥት ጥሰቶች” ታሪክ በግልፅ የሚያሳዩ ማብራሪዎችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ማውጣቱን አስታውሷል።

የህወሃት ቡድን “ህገመንግሥቱን በሚጠብቁት የመከላከያ ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ሆነ ተብሎ የተቀነባበረና አስከፊ ጥቃት በመፈፀም በሃገሪቱ ህግ መሠረት ከፍ ያለ የክህደት ወንጀል ፈፅሟል” ይላል።

ማንም ግለሰብ ወይም አካል በብሄራዊም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሃገሩ ህግ በላይ መሆን እንደማይችልና የኢትዮጵያ መንግሥትም ህግን የማስከበርና ሃገሪቱን የመከላከል ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

መንግሥቱ በአሁኑ ጊዜ ትግራይ ክልል ውስጥ እያካሄደ ያለው ዘመቻ ሁለት ገፅታ ያለው መሆኑን መግለጫው ጠቁሞ አንደኛው የሚያስፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ መድረስ እያረጋገጡ ክልሉን መልሶ መገንባት መሆኑን ይገልፃል። በዚህም መሠረተ ልማቱ እየተጠገነ መሆኑንና ለዜጎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለመስጠት አስተዳደራዊ ሥራዎች መመለሳቸውን አብራርቷል።

መንግሥቱ ሁለተኛ ያለው እንቅስቃሴው ወንጀል የፈፀሙ ሰዎችን ፍትህ ፊት የማቀረቡን ሥራ ማጠናቀቅ መሆኑንና ይህም በክልሉ ውስጥ አሁን እየተከናወነ መሆኑን መግለጫው ይናገራል።

አድማጮች፤ ስፋት ባላቸው የትግራይ ክልል የወቅቱ ሁኔታና ገፅታዎች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ ዘርዘር ያለ ዘገባ ይዘን እንመለሳለን።

XS
SM
MD
LG