የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን አሜሪካ ከአትላንቲክ ባሻገር ካሉት አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግ በመግለጽ፣ አገራቸው ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገሮች ድርጅት (ኔቶ) ጋር ያላትን ህብረት ዳግም እንደምታድስ፣ ብራስልስ ውስጥ ለሁለት ቀናት በተካሄደውና ትናንት ረቡዕ በተጠናቀቀው ስብሰባ ላይ አረጋግጠዋል፡፡
የቪኦኤ ዘጋቢ ኼንሪ ሪጅዌል ከሥራፍው እንደገዘገበው፣ ስብሰባው በቻይና በኩል እየተባባሰ መጥቷል ያለውን አደጋ ጨምሮ በሌሎች በርካታ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ተነጋጋሯል፡፡
ዛሬ ከአትላንቲን ባሻገር ባለው ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ተገልጧል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገሮች ድርጅት ወይም ኔቶን “ጊዜው ያለፈበት” ብለውት ነበር፡፡
የዛሬው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊነክን ግን ከቃልኪዳን አባል አገራቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት በድጋሚ እንዲታደስ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡
እንዲህ አሉ ብሊንከን
የማይናወጠው ቃል ኪዳናችን አብሯችሁ ነው፡፡ አሜሪካ ለኔቶ ሙሉ ለሙሉ ቁርጠኛ የሆነ አቋም አላት፡፡
ብሊንከን የቃል ኪዳን አባል አገሮች ህብረቱን ወይም ኔቶን ስለገጠመው ወታደራዊ ስጋት እንዲህ ብለዋል
“የቤጂንግ ወታደራዊ ፍላጎት በየዓመቱ እያደገ ነው፡፡ ይህም ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ እድገት ጋር የተጣመረ ሲሆን ዛሬ እንደምታውቁት ድሮ የዓለም ግማሽ ክፍል ያህል ሩቅ ይመስሉ የነበሩት አገሮች ዛሬ ሩቅ አይደሉም፡፡ በራሽያ በኩልም እንዲሁ የአባል አገሮቹን ለመፈታተን እና፣ የጋራ ደህንነታችንን የሚያረጋግጠውን መርህ በመተላለፍ ወታደራዊ አቅምን የማሳደግ አዲስ ስትራቴጂ መኖሩን ተመልክተናል፡፡”
የኔቶ ዋና ጸሀፊ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ህብረቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ በመግልጽና ከህበረቱም ጎን ለመቆም ያሳያቸውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
ራሽያ አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ አዳዲስ የኒዩክየር ጦር መሳሪያዎችን ማሰማራቷን ቀጥላለች፡፡ ስለዚህ ስለ ብዙ የጦር መሳሪያዎችም ሆነ እንደ ቻይና ያሉ አገሮችን አስመልከቶ አንድ ስምምነት ማድረግ ይኖርብናል፡፡
ከአውሮፓ ህብረት የደህንነት ተቋማት ጥናት ማዕክለ ሲሞና ሶአሬ፣ ቻይና በኔቶ አባል አገራት ላይ፣ አንጻራዊ የሆነ አዲስ ፈተና መደቀኗን ይገልጻሉ፡፡
“ይህ የኔቶ ወደ ህንድና ፓስፊክ አገሮች የመቀንሳቀስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቁንም የቻይና በአውሮፓ ውስጥ መኖርና እያሳደረች የመጣችውን ተጽእኖ አሉታዊ ጎን ማወቅና እሱን የመቋቋም ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ማለት በእርግጥ፣ ወሳኝ የሆኑ የቴክኖሎጂና የመሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረገውን የውጭውን ቀጥታ ኢንቨስትመንት በበለጠ የመረዳት ነገር ነው፡፡”
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን አሁንም ቢሆን የአውሮፓ ህብረት አጋሮች የመከላከያ ወጭያቸውን እንዲጋሩ ይጠይቃሉ፡፡ ብሊንከን ኔቶ አዲስ እየተደቀነ ያለውን አደጋ መልሶ ለመቋቋም ጠንክሮ መውጣት አለበት፡፡ ካሉ በኋላ ይህ ደግሞ የተዛባ መረጃ መርጨትን፣ የሳይበር ጥቃትን፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ይጨምራል ብለዋል፡፡
በአፍጋኒስታን ያለው የኔቶ ተልእኮም ተነስቷል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር እኤአ ከግንቦት 1 ቀን ጀምሮ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ከታሊባን ጋር ስምምነት ተደርጓል፡፡፡ ብሊነክን ይህ ስምምነት እየተጠና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አስማሚ የሆኑ ንግግሮች የተሰሙ ቢሆንም ውስጣዊ ውጥረቶች በኔቶ ውስጥ መኖራቸውም ተመልክቷል፡፡ ብሊንከ ቱርክ ከራሽያ የገዛችውን ኤስ 400 የመከላከያ መሳሪያ ግዥ እንድታቋርጥ አሳስበዋል፡፡ ቱርክ ግን ስምምነቱ መጠናቀቁን ገልጻለች፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ ከራሺያ ጀርመን ድረስ የተዘረጋውንና ኖርደ ስትሪም 2 የተሰኘውን የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር፣ በግልጽ የምትቃወም መሆኑን ብሊንከን ተናግረዋል፡፡
ቻይና ላይ የተሰነዘሩ በርካታ አሉታዊ ነገሮች ቢኖሩም የአውሮፓ ህብረት ግን ከቤጂንግ ጋር የሚያደርገውን የንግድ ስምምነት እያጠናቀቀ ነው፡፡ ብሊንከን ይህን አስመልከቶ ሲናገሩ
“አጋሮቻችን ከቻያና ጋር ያላቸው ግንኙነት የተወሳሰበ መሆኑንና ሁሌም ፍጹም የተሟላና የተሳካ አለመሆኑ ይገባናል፡፡ ይሁን እንጂ ግን ይህን ፈተና በጋራ እምንወጣበትን መንገድ ማግኘት ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ከአጋሮቻችን ጋር አብረን እየሰራን ቻይና አጋጣሚውን እየተጠቀመች ጫና የምታሳድርባቸውን የቴክኖሎጂና የመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፎች ላይ ያለውን ክፍተት መሙላት ይኖርብናል፡፡
በትናንትናው እለት ከአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የተገናኙት ብሊከን “ የአውሮፓ ህብረት ለዩናይትድ ስቴትስ ቀዳሚው አጋር ነው” ብለው መናገራቸው ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ይሁን እንጂ ተንታኞች እንደሚሉት ከአትላንቲክ ባሻገር ካሉ አገሮች ጋር ያለው አዲሱ ወዳጅነት፣ ህብረቱን የሚገጥሙት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ከፊቱ ተደቅነውበታል፡፡