የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊነክ 20 ከሚደርሱ የላቲን አሜሪካ አገራት መሪዎች ጋር ለመነጋገር ለሁለት ቀን ጉብኘት ፓናማ ገብተዋል፡፡ ብሊንከን ከንግግራቸው በፊት አስቀድሞ በሰጡት መግለጫ ፍልሰት የቀጠናው ብቸኛው ፈተና ሳይሆን ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አስከትለውም ይህን ብለዋል።
"ዩናይትስ ስቴትስ ከሁላችሁም ጋርና በዚህ ጉዳይ ከሚሰሩት ጋር ሁሉ ለመስራት ቁርጠኝነቱ አላት፡፡ ከፍልሰት አንስቶ ህገ ወጥ የሰዎች ማስተላለፊያ መረብን፣ እንዲሁም ውጤታማ የድንበሮችን አስተዳደር ማሻሻልን፣ የተዛቡ መረጃዎችን መቋቋም፣ ለሰዎች ህጋዊ የስደት መንገዶችን ማመቻቸት፣ ጥገኝነት ለሚፈልጉት እንደ ቤታቸው የሚያዩትና ደህንነቱ የተጠበቀ መጠለያ መስጠት ይገኙበታል፡፡ በተለይም ትላልቅና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ማህበረሰቦችን መርዳትና ማረጋጋት ሌላው ነው፡፡ ሥራና ትምህርትን ጨምሮ ስደተኞቹ ህይወታቸውን መልሰው የሚያቋቁመበትን መሳሪያ መስጠት ይኖርብናል፡፡ የምንሰጠው እገዛ እርዳታው የሚያስፈልጋቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በቀጥታ የሚረዳ መሆኑን እርግጠኞች ልንሆን ይገባል፡፡ ለህዝቡ ጤና ደህንነት ማህበራዊ አገልግሎትና የተሻለ መሰረተ ልማት ለሁሉም የሚያጎናጽፍ መሆን ይኖርበታል፡፡"
ብሊንክን ከመሪዎቹ ጋር የሚያደርጉት ንግግር በሚቀጥለው ሰኔ በዩናይትድ ስቴትስ ሎስ አንጀለስ ከሚደረገው ስብሰባ አስቀድሞ የተደረገ መሆኑን ተመልክቷል፡፡