በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ቃለ ምልልስ ከቪኦኤ ጋር


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከቪኦኤ የምሥራቅ አውሮፓ ቢሮ ኃላፊ ሚሮስላቫ ጎንጋድዜ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከቪኦኤ የምሥራቅ አውሮፓ ቢሮ ኃላፊ ሚሮስላቫ ጎንጋድዜ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ

በምሥራቅ አውሮፓ የውጥረትና የዲፕሎማሲ ጥረት ጉዳይ ወደ ዩክሬን የሄዱት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን “ሩሲያ ወደ ግጭት ከመግባት ይልቅ የዲፕሎማሲን መንገድ ትመርጣለች” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ዛሬ ዋና ከተማዪቱ ኪየቭ ላይ ከቪኦኤ የምሥራቅ አውሮፓ ቢሮ ኃላፊ ሚሮስላቫ ጎንጋድዜ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ተናግረዋል።

“በግልፅ የሚሻለውም መንገድ እርሱው ነው” ብለዋል።

ሩሲያ ነገ ተነስታ ዩክሬንን ብትወር ዩናይትድ ስቴትስ ምን ልታደርግ እንደምትችል ሚሮስላቫ ለሠነዘረችላቸው ጥያቄ ብሊንከን ሲመልሱ “በአንድ እጅ የንግግርና የዲፕሎማሲን በሌላው ግጭትና መዘዙን” ይዘው ለሩሲያ ግልፅ ምርጫ ማቅረባቸውን አመልክተው ከሩሲያ ጋር አሁን በቀጥታ፣ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ትብብር ድርጅት /ኔቶ/ ስልታዊ የመረጋጋት ንግግር አማካይነት፣ በአውሮፓ የደኅንነትና ፀጥታ ትብብር ድርጅት /ኦኤስሲኢ/ የኔቶ ሩሲያ ምክር ቤት በኩል ብርቱ የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን እያካሄዱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

“ሩሲያ ዩክሬን ላይ የምታደርገውን ወረራ ለማደስ ብትሞክር ግን አሉ - ብሊንከን - እኛ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሳትሆን፣ እኛ ብዙ ሃገሮች፣ በመላ አውሮፓ ያሉ፤ ከዚያም እንኳ አልፈው ያሉ አንዳንዶች እጅግ በኃይል ምላሽ እንሰጣለን።”

ምላሾቹ በሦስት መንገዶች የሚሰጡ መሆናቸውን የጠቆሙት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከባድ በሆኑ ዝርዝር የገንዘብ፣ የምጣኔ ኃብት፣ የወጭ ንግድ ቁጥጥርና ሌሎችም ማዕቀቦች ላይ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሁለተኛም ለዩክሬን የሚሰጡትን የመከላከያ ወታደራዊ ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ፣ ሦስተኛም ኔቶ እራሱም በምሥራቃዊ ወሰኖቹ ላይ የራሱን መከላከያ እንደሚያጠናክር የማያጠያይቅ መሆኑን አብራርተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ከቪኦኤዋ ሚሮስላቫ ጎንጋድዜ ጋር ኪየቭ ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ዝርዝር ዘገባ በነገ የአየር ሥርጭቶቻችንና በዌብና ማኅበራዊ መገናኛ ገፆቻችን በስፋት እናወጣለን።

XS
SM
MD
LG