የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች 6 ወራት በኋላ ዋሽንግተን ለኪየቭ የምታደርገውን ያልተቋረጠ ድጋፍ የምትቀጥል መሆኑን ለማሳየት አስቀድሞ ባልተገለጸው የጉዞ ፕሮግራማቸው ዛሬ በድንገት ዩክሬን ገብተዋል፡፡
ብሊንከን ለዩክሬንና “ለወደፊቱ የሩሲያ ወረራ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ ለተባሉ” ለሌሎች 18 አገሮች ዩናይትድ ስቴትን የ2.6 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ይፋ አድርገርዋል፡፡
የ2.6 ቢሊዮን ዶላር እርዳታው ከዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስቴር ግምጅ ቤት 675 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን እንደሚያካትት ተመልክቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ብሊንክን ለዩክሬንና በአካባቢዋ ላሉ 18 አገሮች አቅም የሚያጠናክር የውጭ አገር ወታደራዊ ኃይልን ፋይናንስ በማድረግ ስር የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የ2.6 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመትን እንዲፈቅድ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት የሚቀርበውን ጥያቄ ይፋ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
በቅርቡ የነጻነት በዓሏን ላከበረቸውና የህዝቧ ትኩረት የሩሲያን ጦር ወረራ ለመመከት “መልሶ ማጥቃት ላይ ባተኮረበት” በዚህ ወቅት ይህ “ለዩክሬን በጣም ወጤታማ የሆነ አጋጣሚ ነው” ሲሉ አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል፡፡
የብሊንክን የዩክሬን ጉብኝት ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በፊት አስቀድሞ የተካሄደ ጉዞ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት፣ ጉባኤው የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ስለ ግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የሚናገረውን መርሆዎች የዓለም መሪዎች ተሰብስበው አጽንኦት በመስጠት የሚያረጋግጡበት አጋጣሚ ነው ብለውታል፡፡
“ትኩረታችንን የደህንነት እርዳታ ድጋፍ ላይ በማድረግ፣ ዩክሬን በዚህ ጦርነት አሸናፊ ሆና እንድትወጣ መርዳት ነው፣ ወደፊት ድርድር አስፈላጊ ወደሚሆንበት ቀን ስንቃረብ፣ ዩክሬን በጣም ጠንካራ በሆነ አቋም ላይ ትሆናለች” ብለዋል የዩናይትድ ስቴትሱ ከፍተኛው ባለሥልጣን፡፡
ተጨማሪው ወታደራዊ የደህንነት እርዳታው የተለያዩ ዘመናዊ መድፎች ሮኬቶች፣ ተንቃሳቃሽ ከባድ መሳሪያዎችንና ተተኳሾችን እንደሚያካትት ተነግሯል፡፡
ይህ እርዳታም ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የሰጠቸውን ወታደራዊ እርዳታ 13.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያደርሰው ተነግሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣበት ወዲህም እርዳታው 14.2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱም ተመልክቷል፡፡
ዩክሬን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩሲያ በኃይል ወደ ተቀላቀለችው ክሬሚያ የሚገኘውን የሩሲያ ጦር ሠፈር በሚሳዬል መደብደቧን የዩክሬን ጦር አዛዥ ቫለሪ ዛሉዝኒ ትናንት በሰጡት ይፋ መግለጫ አመልክተዋል ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡