የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ዛሬ ሀሙስ በሚያሰሙት አብይ የቻይና ፖሊሲ ንግግር፣ ወሳኝ በሆኑ የመሠረት ልማት ግንባታዎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ፣ ከአጋሮች ጋር በመተባበር፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ደህንነት ለማጠንከርና ያልተጠበቁ ቀውሶችን በመካከል ረገድ፣ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ከቻይና ጋር ለመወዳደር፣ የባይደን አስተስተዳደር ስትራቴጂዎችን ይፋ ያደርጋሉ ተብሉ ይጠበቃል፡፡
ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት አስተዳደሩ ከቻይና “ለመቆራረጥ” እየፈለገ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ አገላለጽ በቀደሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዘመን ይሰማ የነበረ ሲሆን በቻይናና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የንግድ ግንኙነት ቀስ በቀስ ማቋረጥ የሚል ነበር፡፡
የብሊንከን የቻይና ፖሊሲ ንግግር ከመወጣቱ በፊት የገመገሙት አንድ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣን “የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዩናይትድ ስቴት የቻይናን ኢኮኖሚ ከኛ ወይም ከዓለም ኢኮኖሚ ለመነጠል እየፈለገች አለመሆኑን ግልጽ ያደርጋሉ” ብለዋል፡፡
ሌላኛው ከፍተኛ ባለሥልጣንም እንዲሁ “ግልጽ ፍትሃዊና ደህንነታቸው የተጠበቀ እስከሆነ ድረስ በዩናይትድ ስቴትስና በቻይና መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትምነት ግንኙነት በእርግጠኝነት በደስታ እንቀበለዋለን” ብለዋል፡፡
የብሊንከን ንግግር “መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በመተባበርና በመወዳደር” ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ብሉምበርግ ኢክኖሚክስ ያወጣው አንድ ገለልተኛ ጥናት እንዳመለከተው፣ እኤአ ከ1979 ጀምሮ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ኢኮኖሚ፣ በዚህ ዓመት ከቻይናው የዚህ ዓመት ኢኮኖሚ፣ የበለጠ ከፍተኛ ዓመታዊ ዕድገት ለማሳየት መቃረቡን አመልክቷል፡፡
ዋይት ሐውስ ባለፈው ዓመት በሁለቱም ፓርቲዎች ድጋፍ የወጣው የመሠረት ልማት ህግ፣ የመሠረተ ልማት መዋዕለ ንዋይ እና የሥራ ህግ የአሜሪካን መንገዶች ድልድዮችና የባቡር መስመሮች እንደሚያሳድግ የግሽበቱን ጫና እንደሚያቃልል የአሜሪካ ወደቦችን በማሻሻል የአቅርቦት ሰንሰለቱን እንደሚያጠናክር ገልጾ እንደነበር አስታውሷል፡፡
ብሊንክን በ16 ወራቱ የባይደን አስተዳደር፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከአጋሮችና ወዳጆች ጋር በመስራት ዓለም አቀፍ ሥርዓትን ለማሻሻል ስላደረገቸው ጥረት ያብራራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመልክቷል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ቻይና ፉክክር “ስለ አዲሱ ቀዝቃዛ ጦርነት አይደለም” ወይም “ዓለምን ግትር በሆኑ የ ርዕዮተ ዐለም መስመሮች መክፈል” አይደለም ይልቁንም ዓለም አቀፉን ሥርዐት ወደ ቦታው በመመልስና በማደስ ቁልፍ መርሆዎቹ እንዲጠበቁ ለማስቻል ነው” ሲሉ አንደኛው የከፍተኛ የአስተዳደሩ ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስና የእስያ አጋር አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያካሄደቸው ወረራ የዓለም አቀፍ ሥርዐቱን መሠረት ያላካበረ ሲሆን በእስያም ሆነ በየትኛውም ቦታ ያለውን ሁኔታ በኃይል ለመቀየር የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡