በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“የጋዛ የሰላም ድርድር ተጠናክሮ ይቀጥላል” የግብጽ ፕሬዚደንት


የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሊንክን
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሊንክን

የግብጽ ፕሬዚደንት አብደልፋታህ አል ሲሲ “የጋዛው የሰላም ድርድር ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ ተናገሩ፡፡ የግብጹ መሪ ዛሬ ረቡዕ ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንክን ጋር ድርድሮቹ እንዲያንሰራሩ ለማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ተወያይተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሊንክን ወደ ካይሮ የተጓዙት በጋዛ ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት እንደዲረግ የተያዘው ጥረት ሊባኖስ ውስጥ በደረሱት ፍንዳታዎች ሳቢያ ይብሱን አዳጋች እየሆነ በሄደበት በአሁኑ ወቅት ነው፡፡

ሚንስትር ብሊንክን የጋዛ ጦርነት ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሲጓዙ ይህ አስረኛ ጉዟቸው ሲሆን በዚህኛው የዲፕሎማሲ ጉዟቸው ወደ እስራኤልም ይሁን ወደሌላ የአካባቢው ሀገር እንደማይሄዱ ታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብሊንክን እና የግብጽ ፕሬዚደንት ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ የፕሬዚደንቱ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ “ ግብጽ፡ ዩናይትድ ስቴትስ እና ካታር የተኩስ አቁም ድርድሩን እንዲሁም ታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ እንዲሳካ የያዙትን የጋራ ጥረት ለማጠናከር ስለሚቻልበት መንገድ” መነጋገራቸውን አመልክቷል፡፡

ፕሬዚደንት ሲሲ “ወደ ጋዛ ብዛት ያለው እርዳታ እንዳይገባ የሚያሰናክሉ እንቅፋቶችን ለማስወገድ እንዲሁም እስራኤል ዌስት ባንክ ውስጥ የምትፈጽማቸው ጥሰቶች እንዲያበቃ ወሳኝ እርምጃ እንዲወሰድ” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት በግል እንደጠቆሙት ዛሬ ካይሮ ላይ በሚካሄደው ንግግር የሚጠበቅ ውጤት ባይኖርም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጉብኝት እስራኤል እና ሃማስ ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የተያዘው ግፊት እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወደ ካይሮ የተጓዙት ትላንት በሊባኖስ ዙሪያ የሄዝቦላ ተዋጊዎች የሚጠቀሙባቸው በርካታ ኤሌክትሮኒክ የጥሪ መቀባበያ ፔጀሮች መፈንዳታቸውን ተከትሎ መሆኑ ነው፡፡ በፍንዳታው ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ ወደ2800 ገደማ የሚሆኑ ቆስለዋል፡፡ በኢራን የሚደገፈው ቡድን ለፍንዳታው እስራኤልን ወንጅሏል፡፡

እስራኤል በፍንዳታው ዙሪያ አስተያየት አልሰጠችም፡፡

የግብጽ ፕሬዚደንት ጽህፈት ቤት በመግለጫው “ ለሳይበር ጥቃት እየተጋለጠች ያለችውን ሊባኖስን መደገፋችንን በድጋሚ እናረጋግጣለን” ብሏል፡፡ ብሊንክን በካይሮ ቆይታቸው የዩናይትድ ስቴትስ እና የግብጽ ግንኙነት ስለሚጠናከርበት መንገድም እንደሚወያዩ ተጠብቋል፡፡ ሚንስትሩ ከካይሮ ቀጥሎ ስለውይይታቸው ለፈረንሳይ ለእንግሊዝ እና ለጣሊያን አቻዎቻቸው ገለጻ ለማድረግ ወደፓሪስ ያመራሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG