በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ብሊንክን ኒዥር ጉብኝት ላይ ናቸው


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንክን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንክን

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንክን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ዛሬ ወደኒጀር ተጉዘዋል፡፡

ዋሽንግተን ከእስልምና አክራሪ ታጣቂ ቡድኖች ጋር እየተዋጋች ለምትገኘው ለኒዥር ድጋፍ ለመስጠት የምትፈልግ ሲሆን ብሊንከን በጉብኝታቸው ሀገራቸው የመደበችላትን አዲስ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፋ ያደርጋሉ፡፡

አንተኒ ብሊንከን ኒዥርን የጎበኙ የመጀመሪያ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ናቸው፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጋር የተጓዙ ከፍተኛ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች እንዳሉት ጉብኝቱ ዩናይትድ ስቴትስ ለኒዥር በሳህል አካባቢ አጋርነት የሰጠቻትን ስፍራ ይጠቁማል፡፡

ባለሥልጣኑ አክለውም “በሳህል ክልል የተስፋፉትን አደጋዎች በመታገል ረገድ ትክክለኛውን መንገድ መርጠዋል፡፡ ስለዚህ እኛም ያን አዎንታዊ ምሳሌነታቸውን አጉልተን ለማሳየት ጥረት በማድረግ ላይ ነን” ብለዋል፡፡

ወደብ አልባዋ ኒጀር እና አጎራባቾቿን ማሊን፣ ቡርኪና ፋሶን፣ ናይጄሪያን እና ቻድን ጨምሮ ሌሎቹም የሳህል አካባቢ ሀገሮች በሙሉ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ስፋት ያለው ግዛት ተቆጣጥረው የሚገኙትን እስልምና አክራሪ ታጣቂዎችን ለማስወገድ እየታገሉ ናቸው፡፡

የስቴት ዲፓርትመንቱ ባለሥልጣን አክለውም የኒጀርን ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዙምን ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ውስጥ የተካሄዱትን መፈንቅለ መንግሥቶች በመቃወማቸው ያም ብቻ ሳይሆን ጸጥታን በሚመለከቱ ጉዳዮች የሀገራቸውን ፓርላማ ሳያማክሩ በግላቸው የማይወስኑ በመሆናቸው አመስግነዋቸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የኒዥሩ ፕሬዚዳንት ባዙም የማሊ ወታደራዊ መንግሥት ታጣቂዎቹን በመዋጋት እንዲያግዝ የቀጠረውን የሩሲያ ዋግነር ግሩፕ በተመለከተ በግልጽ ተቃውሞ ማሰማታቸውንም አንስተው ባለሥልጣኑ አድንቀዋል፡፡ ማሊ ከዋግነር ግሩፕ የቀጠረቻቸው “አሰልጣኞች” ናቸው ብላ አስተባብላለች፡፡

ማሊ ውስጥ ለአስር ዓመታት ዓለም አቀፍ ኃይል እየመራች የቆየችው ፈረንሳይ በማሊ መሪዎች ጥያቄ ወታደሮቿን ያስወጣች ሲሆን እና በማሊ እና በሌሎቹም በርካታ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ህዝቦች ዘንድ ጸረ ፈረንሳይ ስሜት እየተባባሰ መጥቷል፡፡

ጋና እንዳስታወቀችው ቡርኪና ፋሶም ከሩሲያው ዋግነር ተዋጊዎች ቀጥራለች፡፡ የቡርኪናው ወታደራዊ አገዛዝ ከማረጋገጥም ከማስተባበልም ተቆጥቧል፡፡

“ዋግነር ይበልጡን በንቃት የሚንቀሳቀሰው ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው፡፡ ጸረ ፈረንሳይ ስሜት ስላለ በዚያ እየተጠቀሙበት ይመስለኛል” ሲሉም

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን አክለዋል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በቀጣናው ፈረንሳይ በምትታይበት መንገድ ሳይሆን አዎንታዊ ገጽታ ያላት መሆኑን ባለሥልጣኑ ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG