የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ ገቡ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ኪቭ የገቡት ዩክሬን በሩሲያ ኢላማዎች ላይ የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን መጠቀም እንዲፈቀድላት ምዕራባውያንን በመጎትጎት ላይ ባለችበት ወቅት ነው፡፡
ከፍተኛ ዲፕሎማቶቹ ዛሬ ረቡዕ ከፖላንድ በባቡር ተጉዘው ዩክሬን መዲና ኪቭ የገቡት፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ምክትክል ፕሬዝዳንት ከማላ ሃሪስና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ በትላንቱ ፕሬዝዳታዊ ክርክራቸው ሁለት ዓመት ተኩል የፈጀውን የዩክሬኑን ጦርነት ጉዳይ አንስተው ከተከራከሩ በኋላ ነው፡፡
ብሊንከን ወደ ዩክሬን ከማምራታቸው አስቀድሞ ለንደን ውስጥ በሰጡት መግለጫ “ኢራን የአጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳይሎችን ለሩሲያ ሰጥታለች። ይህም ጦርነቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲባባስ የሚያደርግ ርምጃ ነው” ሲሉ ኢራንን ከሰዋል፡፡
ዩክሬን ዩናትይድ ስቴትስን እና አጋሮቿን የሩሲያን ኢላማዎች ለማጥቃት የሚያስችላትን የረዥም ርቀት መሳሪያዎችን ስትጠይቅ ቆይታለች። ሩሲያ በቅርቡ አዲስ የጦር መሳሪያ አግኝታለች መባሉ ከተሰማ ወዲህ ደግሞ ዩክሬይን ጥያቄውን አጥብቃ ትገፋበታለች የሚል ግምት አሳድሯል።
የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽሚሃል ሲቪሎችን እና መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ ዩክሬን የረጅም ርቀት ማጥቂያ መሳሪዎችን የመጠቀም ፈቃድ በቅርቡ እንደምታገኝ ያላቸውን ተስፋ ገለጸዋል።
ባይደን ዩክሬን ራሷን ለመከላከል በድንበር በኩል ወደ ሩሲያ ዘልቀው የሚገቡ ከዩናይትድ ስቴትስ የተሰጧትን ሚሳይሎች እንድትተኩስ ፈቅደውላታል፡፡ ይሁን እንጂ ግጭቱ የበለጠ እንዳይባባስ ስጋት በመፍጠሩ የሚሳይሎቹ የተኩስ ርቀት መጠን በእጅጉ ተገድቧል።
ብሊንከንና ላሚ ኪቭ እንደደረሱ፣ ብሪታኒያ፣ ‘ዓለም አቀፉን ማዕቀብ በመጣስ የሩሲያን ነዳጅ ዘይት አጓጉዘዋል’ ያለቻቸውን 10 የንግድ መርከቦች የእንግሊዝን ወደቦችን እንዳይጠቀሙ አግዳለች፡፡
መድረክ / ፎረም