የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ ሃገሮች ባደረጉት ጉብኝት ማጠቃለያ ትናንት፤ ሐሙስ ርዋንዳ ነበሩ።
ብሊንከን በየሄዱበት ሃገር “አሜሪካ የአፍሪካ እውነተኛ አጋር መሆን እንደምትፈልግ፣ ግጭቶችን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ፣ ሃገሮች ከማን ጋር መወዳጀት እንዳለባቸው ትዕዛዝ ሰጪ መሆን እንደማትፈልግ” አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከርዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር ኪጋሊ ላይ ተወያይተዋል።
የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና በጣም ያሳሰቧቸውን ጉዳዮች በውይይቱ ወቅት ማንሳታቸውን ብሊንከን ለሪፖርተሮች አመልክተው ርዋንዳ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ውስጥ ያሉ አማፂያንን መደገፍ እንድታቆም አሳስበዋል።
“ሁሉም ወገኖች የታጠቁ ቡድኖችን እንደሚደግፉ፤ ኮንጎም “የዴሞክራሲ ኃይሎች ለርዋንዳ አርነት” የሚባለውን ቡድን እንደምትደግፍ፤ ሩዋንዳም የኮንጎውን አማፂ ኤም-23ን እንደምትደግፍ ተዓማኒ ሪፖርቶች አሉ። የኛ አቋም ግልፅ ነው፤ በማንም ይሁን በማን ለየትኛውም ታጣቂ ቡድን የሚሰጠው ድጋፍ መቆም አለበት” ብለዋል ብሊንከን።
ከትናንት በስተያ ደግሞ “ርዋንዳ ምሥራቅ ኮንጎ ያሉ ኤም-23 የሚባሉትን ታጣቂ አማፂያን ትደግፋለች” መባሉ እንደሚያሳስባቸው ብሊንከን ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሽሳ ውስጥ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረው ነበር።
የኮንጎው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፍ ሉቱንዱላ ደግሞ “በሃገራችን በስተምሥራቅ ያለው አካባቢ ላለፉት ሃያ ዓመታት በአሸባሪዎች መከራውን አይቷል፤ ሕዝባችን ተፈጅቷል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነው በሁለትዮሽ ጉዳይ ላይ ሃሳብ የተለዋወጥነው” ብለዋል።
ብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ሰኞ በደቡብ አፍሪካ የጀመሩት ተማሪዎች ከአፓርታይድ አገዛዝ ጋር ያደረጉትን ትግል የሚያሳየውን “የሶዌቶ አመፅ” ቤተመዘክር በመጎብኘትና ለተማሪዎቹም ክብር በመስጠት ነበር።
ብሊንከንና የደቡብ አፍሪካው አቻቸው ናለዲ ፓንዶር የጋራ ግብና ፍላጎታቸውን በተመለከተ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ሁለቱም ወገኖች ተናግረዋል።
ሃገራቸው ቻይናና ሩሲያ አፍሪካ ላይ ካላቸው ተፅዕኖ ጋር ‘ፉክክር ውስጥ ነች’ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ የተናገሩት ብሊንከን ስለ ጉብኝታቸው አጠቃላይ ዓላማ ሲያብራሩ “ከምንም በላይ የምንፈልገው በዩናይትድ ስቴትስና በአፍሪካ መካከል እውነተኛ ትብብር እንዲኖር ነው። ሚዛኑን ያልጠበቀ ወይም የእንካ በእንካ ግንኙነት አንፈልግም። ከአፍሪካ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖረን የምናሳየው ቁርጠኛነት ማንንም ለመብለጥ ብለን የምናደርገው አይደለም” ብለዋል።
የብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝት የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭን ጉብኝት ተከትሎ የመጣ ነው።
አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ፉክክር ላይ አለመሆኗን አፍሪካዊያን ስለማመናቸው የሺካጎ ዓለምአቀፍ ጉዳዮች ምክር ቤቷ ኤሊዛቤጥ ሻክልፎርድ እርግጠኛ አይደሉም።
“ይህ ኃያላን ሃገሮች የሚያደርጉት የፉክክር ጨዋታ ነው፤ በቦታው ካልተገኘን እንረሳለን የሚል ፍርሃት አለ። ሩሲያና ቻይና ትኩረት የሚሰጧቸው ቦታዎች ላይ ልንረሳ እንችላለን የሚል ፍራቻ አለ” ሲሉ ለቪኦኤ ተናግረዋል ሻክልፎርድ።
ሌላው ለቪኦኤ ሃሳባቸውን ያካፈሉት ባለሙያ ቶም ሺሂ ‘የባይደን አስተዳደር አፍሪካን የሚያይበት መንገድ ተቀይሯል’ ባይ ናቸው።
“እንደሚመስለኝ ከቀደመው አስተዳደር ጋር ያለው ልዩነት የባይደን አስተዳደር አፍሪካዊያን እንዴትና ከማን ጋር ጉዳያቸውን ማከናወን እንዳለባቸው ለመንገር ፍላጎት የለውም። የቀደመው አስተዳደር ቻይናን በተመለከተ የሰላ መልዕክት ሲያስተላልፍ ነበር” ብለዋል ሺሂ።
ኤሊዛቤጥ ሻክልፎርድ ደግሞ “አሜሪካ በቅርቡ ምርጫ አካሂዳ ወደ ዴሞክራሲ አቅጣጫ እየተጓዘች እንዳለችው እንደ ኬንያ ላሉ ሃገሮች ትኩረትና ቅድሚያ መስጠት አለባት፤ አህጉሪቱ ውስጥ በየቦታው እየተገኘች ከሌሎች ጋር መፎካካር እንዳለባት አይሰማኝም” ብለዋል።
ብሊንከን ባለፈው ኅዳር ኬንያን፣ ሴኔጋልንና ናይጄሪያን ጎብኝተው ነበር።