“ፑቲን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መንግሥት ማስወገድ ከተሳካላቸው ዩክሬን ውስጥ የሰብዓዊ መብቶችና ሰብዓዊ ሁኔታው ቀውስ ይባባሳል” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን አስጠንቅቀዋል።
ብሊንከን ዛሬ ጄኔቫ ላይ እየተካሄደ ላለው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በቪድዮ ባደረጉት ንግግር “የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ሆን ብለው ባቀናጁት የዩክሬን ወረራ ተጠያቂ ሳይሆኑ ከቀሩ ሰላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚረዱት የዓለምአቀፍ ሥርዓት ደንቦች ይዳከማሉ” ብለዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደእማኝ ያነሷት ክሪምያ በሩሲያ ከተያዘች ወዲህ ከህግ ውጭ የሚካሄዱ ግድያዎች፣ የሰዎችን ደብዛ በኃይል ማጥፋት፣ የስቃይ አያያዝ፣ የዘፈቀደ እሥራቶች፣ የሕዳጣን ጎሣዎችና እምነቶች አባላትን ማሳደድ፣ ተቃውሞን እጅግ አስከፊ በሆነ መንገድ ማፈን መበርከታቸውንና በሩሲያ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎችና ዓለምአቀፍ የሰብዓዊነት ህግጋት ጥሰቶች ሪፖርቶች በየሰዓቱ እየተካበቱ መምጣታቸውን አመልክተዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን ከስድስት ቀናት በፊት ከወረረች አንስቶ በሲቪሎችና በሲቪል የመሠረተልማት አውታሮች ላይ ድብደባዎች መጠናከራቸውን በመግለፅ የከሰሱት ብሊንከን ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች የመኖሪያ ህንፃዎች ዒላማ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለሚሊዮኖች የመጠጥ ውኃ የሚያድርሱ እጅግ አስፈላጊ መዋቅሮችና በክረምቱ ምክንያት ወደ በረዶነት እንዳይለወጡ ለማሞቅ የሚረዱ፣ ብርሃን የሚሰጡ የኤሌክትሪክ ተቋማት መውደማቸውንም ጠቁመዋል።
ትናንት ብቻ በሩሲያ ጥቃት ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ አንድ መቶ ሲቪሎች መገደላቸውን፣ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸውንና ትክክለኛዎቹ ቁጥሮች ከዚያም በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከፍተኛ ኮሚሽነሯ ማስታወቃቸውን ብሊንከን አስታውሰው በጥቂት ቀናት ውስጥ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዩክሬናዊያን ከሃገራቸው መሰደዳቸውንና ህፃናት፣ አረጋዊያን፣ የአካል ጉዳተኞች በግጭት ቀጣናዎች ውስጥ እጅግ አደገኛ ለሆነ ጉዞ መዳረጋቸውን ገልፀዋል።
የሩሲያ ወታደሮች በሲቪል መዋቅሮችና በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ጥቃት እንደማያደርሱ ክሬምሊን ቤተ መንግሥት ዛሬ አስታውቋል።
የዩክሬን ስደት በዚህ ክፍለ ዘመን ግዙፉ የአውሮፓ ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚሆን የሚናገረው የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር አራት ሚሊየን ዩክሬናዊያን ይሰደዳሉ በሚል እየተዘጋጀ መሆኑን ማስታወቁን ሊሳ ሽላይን ዘግባለች።
አንተኒ ብሊንከን በዛሬው ንግግራቸው “የሩሲያ አፈና ዩክሬን ድንበሮች ላይ አይቆምም፤ ክሬምሊን ሩሲያ ውስጥም የሚያካሂደውን ጭቆና እያበረታ ነው፤ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ የፑቲን የፖለቲካ ተቀናቃኞች ለተራዘመ ጊዜ ተዋክበዋል፣ እንዲሸማቀቁ ተደርገዋል፤ ተመርዘዋል፤ ታስረዋል” ሲሉ ከስሰዋል።
እንዲህ ዓይነቱ አያያዝ የዩክሬንን መወረራ በሰላማዊ ሁኔት በሚቃወሙ ላይም እየተካሄደ መሆኑን ብሊከን ጠቁመው በሺሆች የሚቆጠሩ መያዛቸውን፣ የውጭ ሃገርን ወይም ድርጅትን የሚረዳ ማንም ሰው እስከ ሃያ ዓመት እሥራት እንደሚፈረድበት ተናግረዋል።