ዋሺንግተን ዲሲ —
የመን አደን አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን እና ከደርዘን በላይ የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የደህንነት ምንጮች ገለፁ ለሮይተርስ ተናገሩ። አደጋው የደረሰው አዲስ የተቋቋመውን የየመን መንግሥት የካቢኔ አባላት ከሳዑዲ አረቢያ የጫነው አውሮፕላን የመን ሲያርፍ መሆኑ ታውቋል።
ልክ አውሮፕላኑ አየር ማረፊያ ውስጥ ሲያርፍ ከፍተኛ የፍንዳታ እና የተኩስ ድምፅ መሰማቱን በአካባቢውየነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
የየመን ጠቅላይ ሚኒስትር ሚን አብዱልማሊክና በሳዑዲ አረቢያ የየመን አምባሳደር ሞሐመድ ሰኢድ አልጃባርን ጨምሮ አዲሶቹ የካቢኔ አባላት በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ቢሆንም ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት እንዲሳወሩ መደረጉን የሳዑዲ ጋዜጦች ዘግበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም “ሁላችንም የካቢኔ አባላት በአደን በደህና ሁኔታ ላይ እንገኛለን” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ ከጥቃቱ መትረፋቸውን አረጋግጠዋል። አያይዘውም በአደን አየር መንገዱ ላይ በአሸባሪዎች የተሰነዘረው ጥቃት በየመን እና በሕዝቦቿ ላይ የተሰነዘረ ነው ብለዋል።