በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኦሳማ ቢን ላድን መገደል ለዓለም ሠላም ትልቅ አንድምታ አለው


ኦሳማ ቢንላድን ቢገደልም የሽብር ንቅናቄው አልቃይዳ ሞተ ማለት አይደለም።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር መስከረም 11 ቀን 2001 ዓም ሽብርተኞች አሜሪካ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ጥለው ወደ ̎ሦስት ሺህ የሚሆን ሰዉ ከገደሉ ወዲህ፣ የአሜሪካ ባለስልጣናት ”በህይወት ይሁን በሞት” በማለት ኦሳማ ቢን ላድንን ሲፈልጉ ነበር። ቢን ላድን የመሠረተውና የሚመራው የሽብርተኞች መረብ አልቃይዳ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለምሳሌ በኩዌትና በሳኡዲ አረቢያ፣ በአፍሪቃ በኬንያና በታንዛኒያ እንዲሁም በበርካታ የአዉሮፓ አገሮች ለደረሱ ጥቃቶች ተጠያቂ በመሆኑ መገደሉ፣ ለዓለም ሰላም ከፍተኛ አንድምታ እንዳለው በሞንትሪያል-ካናዳ የኮንካርዲያ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪቃ ፖለቲካ መምህር ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ ገልጸውልናል።
የሆነ ሆኖ የቢን ላድን ተከታዮች መሪአቸው ባመነበት ጸንቶ ህይወቱን እስከማጣት በመድረሱ እንደሰማእት ይቆጥሩታል፣ በዓለም ላይ የአጸፋ ጥቃት ሊያደርሱ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል። በተለይም በአልቃይዳ የሥልጣን እርከን ሁለተኛው ሰውና ዋናው የንቅናቄው ፍልስፍና አፍላቂ ግብጻዊው ምሁር አልዘዋሪ መሆኑን ገልጸው ድርጅቱ የሽብር ሥራውን መቀጠሉ አጠያያቂ አይደለም ብለዋል። የንቅናቄው አባላት መንግሥት አልባ ወደሆኑ እንደሶማሊያ ወዳሉ አገሮች በመሄድ የምስራቅ አፍሪቃ አገሮችን ሊያጠቁ ስለሚችሉ ጥብቅ ጥንቃቄ እንደሚያሻም መክረዋል። ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ ስለኦሳማ ቢን ላድን መገደል አንድምታ ለትዝታ በላቸው የሰጡትን ሙሉ ግምገማ ያዳምጡ።

XS
SM
MD
LG