በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን እና ትረምፕ የመጀመሪያውን ክርክር ነገ ያደርጋሉ


ፎቶ ፋይል፦ ይህ የፎቶ ጥምረት በወቅቱ የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና የቀድሞ ምክትል ፕሬዘዳንት ጆ ባይደንን የመጀመሪያው ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ያሳያል፤ ክሊቭላንድ እአአ መስከረም 29/2020
ፎቶ ፋይል፦ ይህ የፎቶ ጥምረት በወቅቱ የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና የቀድሞ ምክትል ፕሬዘዳንት ጆ ባይደንን የመጀመሪያው ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ያሳያል፤ ክሊቭላንድ እአአ መስከረም 29/2020

በአሜሪካ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እጩዎች የሆኑት ዲሞክራቱ ጆ ባይደን እና ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትረምፕ የመጀመሪያውን ክርክራቸውን ነገ ሐሙስ ማምሻውን አትላንታ በሚገኘው የሲኤንኤን ስቱዲዮ ያደርጋሉ።

በክርከሩም ከራሳቸው ይልቅ የተቀናቃኛቸው መመረጥ ለሃገሪቱ አደጋ መኾኑን ለአሜሪካ ሕዝብ ለማስረዳት ይሞክራሉ።

ባይደን ሃገሪቱን እያቆረቆዙ ናቸው በማለት ትረምፕ ሲከሱ ሰንብተዋል። የዋጋ ግሽበትና ወንጀል በሃገር ውስጥ፣ በውጪ ደግሞ በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ በመካሄድ ላይ ያሉትን ጦርነቶች በመጥቀስ ባይደን አሜሪካንን ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እያቀረቧት ነው በማለት ትረምፕ ይከሳሉ።

ባይደን በበኩላቸው ትረምፕ ሃገሪቱን ወደ ኋላ ሊመልሱ እየሞከሩ ነው ሲሉ ይከሳሉ። ታይተዋል ያሏቸው መሻሻሎች እና መልካም ሁኔታዎችም ትረምፕ የሚመረጡ ከሆነ አደጋ ላይ ይወድቃሉ ሲሉ ይተቻሉ።

ሁለቱ እጩዎች ተቀራራቢ ድጋፍ እንዳላቸው የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች በማመልከታቸው፣ የነገውን ክርክር አጓጊ አድርጎታል። ክርክሩ ለሁለቱም እጩዎች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ቢሆንም፣ በተቃራኒው ደግሞ አደጋም ሊኖረው እንደሚችል ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።

ሁለቱም እጩዎች ክርክሩን የሚያደርጉት በፓርቲዎቻቸው በይፋ በእጩነት ከመቅረባቸው በፊት ነው። በክርክሩ ወቅት በአካል ተገኝተው የሚከታተሉ ታዳሚዎች የማይኖሩ ሲሆን፣ የመክፈቻ ንግግር እንደማይፈቀድ ታውቋል። ተረኛ ያልሆነው ተናጋሪ መነጋገሪያ፣ ተራው እስኪደርስ እንደሚዘጋ የክርክሩ አስተናጋጅ የሆነው ሲ ኤን ኤን አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG