የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን ትናንት ኅሙስ እንዳመለከቱት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሀገራቸው ለጋዛው ጦርነት የምትሰጠው ቀጣይ ድጋፍ ‘የሲቪሎችን እና የረድኤት ሠራተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ በሚወሰዱ አዳዲስ ርምጃዎች የሚወሰን ይሆናል’ ሲሉ ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ነግረዋቸዋል።
ባይደን በብራስልሱ የኔቶ የመሪዎች ጉባኤ ወቅት ከኔታንያሁ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ብሊንከን ብራስልስ ላይ በተካሄደ ጋዜጣዊ ጉባኤ ወቅት አመልክተዋል። “በሰብአዊ ረድኤት ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እና በጋዛ ያለው አጠቃላይ የሰብአዊ ሁኔታ ተቀባይነት እንደሌለው ነግሯቸዋል” ብለዋል።
ባይደን ይህን ያሉት እስራኤል በቅርቡ በጋዛ ያካሄደችው የአየር ድብደባ ሰባት የረድኤት ሠራተኞችን የገደለው ጥቃት ውጥረት እየጎላበት የመጣውን የሁለቱን መሪዎች ግንኙነት ይበልጥ እያሻከረው መሆኑ እየተነገረ ባለበት ጊዜ ነው። ብሊንከን አክለውም ባይደን “አፋጣኝ የተኩስ አቁም አስፈላጊ መሆኑን መናገራቸውን ገልጠዋል።
በተጨማሪም ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ ለማድረስ እርምጃዎች ቢወሰዱም "በተጨባጭ የሚታየው ውጤት ግን አሳዛኝ እና ተቀባይነትም የሌለው ነው" ብለዋል።
መድረክ / ፎረም