በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፕሬዚዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጡ


ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተባባሰ የመጣው ጥቃት፣ የክልሎችና የጎሳ ክፍፍል እጅግ ያሳሰባቸው መሆኑን ትናንት ረቡዕ፣ ምሽቱ ላይ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ “በትግራይ ውስጥ በስፋት እየተፈጸመ ያለውን የጾታ ጥቃት ጨምሮ እየተስፋፋ ያለው መጠነ ሰፊው የሰብአዊ መብት ጥሰት መቆም አለበት”ም ብለዋል፡፡

ዋይት ሀውስ ከሚገኘው ጽ/ቤታቸው ባወጡት መግለጫቸው፣

“በአገራቸው ከየትኛውም ወገንም ሆነ ብሄር የተወለዱ ቤተሰቦች በአገራቸው ውስጥ በሰላምና በደህንነት መኖር ይኖርባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ጠባሳዎች በመሣሪያ ኃይል ሊድኑ አይችሉም፡፡” ያሉት ፕሬዚዳንቱ “ትግራይ ውስጥ ያሉ ታጣቂ ኃይሎች የተኩስ አቁም ማወጅና ተግባራዊ ማድረግ፣ የኤርትራና የአማራ ኃይሎችም ለቀው መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡” በማለት አሳስበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:44 0:00


ፕሬዚዳንቱ “በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እየተራዘመ በመጣው ግጭት የተነሳ ኢትዮጵያ እኤአ ከ1980 ወዲህ የመጀመሪያውን የረሀብ አደጋ ሊገጥማት እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡” ያሉ ሲሆን

“ሁሉም ወገኖች በተለይም የኢትዮጵያና የኤርራት ኃይሎች የረሀብ አደጋው በክልሉ እንዳይስፋፋ ለመከላከል እንዲቻል ምንም ዓይነት ገደብ ያልተደረገበት የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር መፍቀድ አለባቸው፡፡” በማለት አሳስበዋል፡፡

ባይደን በመግለጫቸው “ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ መሪዎች እና ተቋማት የእርቅና የሰብአዊ መብት እንዲያጠናክሩና ብዝሃነትን እንዲያከብሩ ታሳስባለች፡፡ ያንንም ማድረግ የአገሪቱን ህብረትና የግዛት አንድነት የሚያሰፍን ሲሆን የኢትዮጵያንም ህዝብ ደህንነትም ያረጋጣል፣ በአጣዳፊ የሚያስፈልገውም እርዳታ በወቅቱ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡” ብለዋል፡፡

“የኢትዮጵያ መንግሥትና በፖለቲካው ዘርፍ ያሉት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሁሉንም ወገኖች የሚያሳትፍ ውይይቶችን በማድረግ አለባቸው፡፡” በማለት ጥሪያቸውን ያስተላለፉት ባይደን

“ የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ በመሥራት፣ ለጋራ ህልሞቹንና፣ ለአገሪቱ መጻኢ የፖለቲካ እድል፣ ዘላቂና እኩልነት የሰፈነበት የኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግና መሠረት ሊጥል ይችላል፡፡” ብለዋል፡፡

አያይዘውም “ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን የሁለቱን አገሮች የረጅም ጊዜ ግንኙነትና ትብብር መሠረት በማድረግ፣ እንዲሁም ከሌሎች የአፍሪካ ህብረት፣ ከዓለም መንግሥታትና ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር በመሆን ኢትዮጵያ እነዚህ ችግሮች እንድትፈታ ለመርዳት ቁርጠኝነቱ አላት፡፡” ሲሉም ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

“በምስራቅ አፍሪካ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍ ፌልትማን አወዛጋቢ የሆነውንና የሁሉንም ወገኖች ፍላጎት ማሟላት ያለበትን የኢትዮጵያን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጨምሮ፣ በቀጠናው ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሁሉንም ወገኖች በሚያሳትፍ መልኩ መፍትሄ ለማስገኘት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ዳግም የታደሰውን የዲፕሎማሲ ጥረት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡” ያሉት ባይደን

“ልዩ ልኡኩ ፌልትማን ወደ ቀጠናው በሚቀጥለው ሳምንት ተመልሰው የሚሄዱ ሲሆን የደረሱበትንም ውጤት እየተከታተሉ ያሳዉቁኛል፡፡” ብለዋል፡፡

ባይደን በመጨረሻም “የአሜሪካ ዲፕሎማሲ እሴቶቻችን ያንጸባርቃል” በማለት ይህም “ ነፃነትንን መመከት፣ ሁሉን አቀፍ መብቶችን መጠበቅ፣ የህግ የበላይነት ማክበርና እያንዳንዱ ሰው ሰብእና በክብር መያዝን” እንደሚያካትት ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በሰጡት መግለጫ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው ያልተሳካ መሆኑ እየገለጽን፣ ወደፊት እንደንደረስን የምናቀርብ መሆኑን እናስታውቃለን ፡፡

XS
SM
MD
LG