የ81 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ የአዕምሮም ሆነ የጉልበት ብቃታቸውን ትላንት ምሽት በተካሄደው ክርክር ላይ እንደሚያሳዩ በደጋፊዎቻቸውና ፓርቲያቸው ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም፣ በትልቁ የአሜሪካ ፖለቲካ መድረክ ላይ ግን የተጠበቀውን ብቃት ሳያሳዩ ቀርተዋል።
ፕሬዝደንት ባይደን ትላንት ምሽት ከሪፐብሊካኑ እጩ ዶናልድ ትረምፕ ጋራ ያደረጉት ክርክር እንዳበቃ ነበር አጋሮቻቸው፣ የፓርቲው ስትራቴጂ አውጪዎች እንዲሁም ድምፅ ሰጪዎች በምርጫ ፉክክሩ ብቁ ሆኖ የመቀጠላቸው ጉዳይ ያሰጋቸው።
በክርክሩ ወቅት ባይደን በተደጋጋሚ ሲደነቃቀፉ፣ ዝም ሲሉ፣ አንዳንድ ጊዜም የሚሉትን ለመረዳት በሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ተስተውሏል።
የዲሞክራቲክ ፓርቲው ዓባላት፣ በይፋም ሆነ በሚስጥር፣ ፓርቲው ባይደንን በሌላ እጩ መተካት አለበት የሚል ጥያቄ በማንሳት ላይ ናቸው።
“አጀማመሩ ዘገምተኛ ነበር፣ ይህ ለሁሉም ግልጽ ነው። በዚህ ላይ ሙግት አልገጥምም” ሲሉ ከክርክሩ በኋላ ለሲ ኤን ኤን የተናገሩት ምክትል ፕሬዝደንት ካመላ ሄሪስ፣ “በኅዳር ወር የምናደርገው ምርጫ፣ በሕይወት ዘመናችን ወሳኝ የሆነ ምርጫ ነው” ሲሉ አክለዋል።
በባይደን ደካማ የክርክር አፈጻጸም የሪፐብሊካኖቹ ወገን ደስታ ከመጠን በላይ እንደነበር ያወሳው የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ፣ የትረምፕ ምርጫ ዘመቻ ሃላፊ ግን፣ ባይደን ሊተኩ ይችላሉ የሚለውን ወሬ አጣጥለዋል። “ያ ሊሆን የሚችለው ባይደን በፈቃዳቸው ከለቀቁ ብቻ ነው። ባይደን ደግሞ ይህን አያደርጉም” ሲሉ ተደምጠዋል የትረምፕ ምርጫ ዘመቻ ከፍተኛ አማካሪ ክሪስ ላሲቪታ።
የክርክሩን ፍጻሜ ትከትሎ ከሪፖርተሮች ጋራ የተገናኙት የባይደን አማካሪዎች፣ በፕሬዝደንቱ ደካማ የክርክር አፈጻጸም ላይ ሳይሆን፣ ትረምፕ በክርክሩ ወቅት ዋሽተዋል ያሏቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አቅርበዋል።
መድረክ / ፎረም