በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፕሬዚዳንት ባይደን እና ፕሬዚዳንት ፑቲን ጉባዔያቸውን ጀምረዋል


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እና የሩስያ ፕሬዚደንት ቪላዲሚር ፑቲን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እና የሩስያ ፕሬዚደንት ቪላዲሚር ፑቲን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እና የሩስያ ፕሬዚደንት ቪላዲሚር ፑቲን በከፍተኛ ደረጃ ሲጠበቅ የቆየውን ጉባዔያቸውን ስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቫ ውስጥ ጀምረዋል።

ስዊስ ጉባኤውን እንድታስተናግድ የተመረጠችው ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የራቀ ታሪክ ስላላት ሲሆን ሁለቱ መሪዎች እንደተገናኙ ጋዜጠኞች ፊት በነበራቸው አጭር ቆይታ በዩናይትድ ስቴትስ እና ሩስያ ጋዜጠኞች ግፊያና ትርምስ መሃል ባጭሩ ምስጋና ምስጋና ተለዋውጠዋል።

"ሚስተር ፕሬዚደንት ዛሬ ጉባኤችንን እንድናደርግ ስላሳዩት ተነሳሽነት አመሰግንዎታለሁ፤ ጉዞዎ ረጅም እንደነበር አውቃለሁ፤ ዩናይትድ ስቴትስ በከፍተኛ ደረጃ እንዲነጋገሩባቸው የሚያስፈልጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ፤ ስብሰባችን ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል ፑቲን ባይደንን በአስተርጓሚ።

ፕሬዚደንት ባይደን በበኩላቸው "አመሰግናለሁ ቅድም ውጪም እንዳልኩት፣ ምንጊዜም ቢሆን በግንባር መገናኘቱ ነው የሚሻለው" በማለት መልሰዋል።

ሁለቱም ወገኖች በንግግራቸው የትብብር ተስፋ እንደሚኖር ሲያሰምሩበት ቆይተዋል፤ ሆኖም ውጥረት በተሞላበት የሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት የሚል ጉጉት ላለመቀስቀስ ጥረት አድርገዋል።

ይልቁንም የሁለቱ መሪዎች ንግግር ይበልጡን ያሉ ቅሬታዎችን የሚያሰሙበት ከመሆን ባለፈ ትልቅ ስምምነት ይወጣዋል ተብሎ አይጠበቅም።

አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን በፕሬዚዳንት ባይደን የስዊዘርላንድ ጉዞ ኤር ፎርስ ዋን አውሮፕላን ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ብዙ የጎላ ውጤት የሚጠበቅበት አይደለም ብለዋል።

የሩስያው ፕሬዚዳንት ጄኔቫ እንደረሱ ወዲያውኑ ወደጉባኤው ስፍራ የተጓዙ ሲሆን ፕሬዚዳንት ባይደን ጉባኤው ቦታ የደረሱት ከፑቲን በኋላ ነው።

ይህም እአአ በ2018 የሩስያው ፕሬዚዳንት ሄልሲንኪ ላይ ቀድመዋቸው የተገኙትን የወቅቱን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕን ከግማሽ ሰዓት በላይ ያስጠበቁበት ሁኔታ እንዳይደገም ዋይት ሃውስ የዲፕሎማሲዊ መላ እንደሆነ ተገልጿል።

ሁለቱ መሪዎች ከተጨባበጡ በኋላ ወደስብሰባቸው የገቡ ሲሆን መጀመሪያ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንን ፕሬዚዳንት ፑቲን ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ሰርጌይ ላቭሮቭን ይዘው ስብሰባቸው ያካሂዳሉ፥ ሁለቱም አስተርጓሚዎች ይኖሩዋቸዋል።

ከመጀመሪያው አጭር ስብሰባ በኋላ ሁለቱም መሪዎች ተጨማሪ ልዑካናቸውን ይዘው ውይይታቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንዳሉት ከሆነ ቢያንስ አራት ሰዓት ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።

XS
SM
MD
LG