በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን ከኮቪድ የህመም ምልክቶቻቸው በእጅጉ እያገገሙ መሆናቸውን ሀኪሞቻቸው ተናገሩ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን "የነበሯቸው የኮቪድ-19 የህመሙ ምልክቶች በጠቅላላ ማለት በሚያስችል ደረጃ ተወግደውላቸዋል" ሲሉ ሐኪማቸው ተናገሩ።

ትናንት ፕሬዚዳንት ባይደን "ከቀን ወደቀን እየተሻለኝ ነው" ብለዋል።

ዋይት ኃውስ በጣም ተላላፊ የሆኑትን የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች በደንብ ሊከላከሉ የሚችሉ አዳዲስ የክትባት ዐይነቶች መስራት ስለሚቻልበት መንገድ የሚወያይ ጉባዔ ዛሬ ለማካሄድ ማቀዱን አስታውቋል።

"ደህና ነኝ፥ ድምጼ አሁንም እንደሻከረ ነው። በየቀኑ ጠዋት እና ከሰዓት በኋላ፤ ማታም ሙሉ ምርመራ እየተደረገልኝ ነኝ፣ የሰውነት ሙቀት የደም ውስጥ ኦክሲጂን መጠን፣ የልብ ምት ሁሉም ዓይነት ምርመራ ይደረግልኛል፣ እስካሁን ሁሉ ነገር ጥሩ ነው። ስለዚህ ከቀን ወደቀን እየተሻለኝ ነው።

አሁንም በጥቂቱ ጉሮሮዬ ላይ የህመም ስሜት እና ሳል አለኝ፥ ግን እሱም በጣም እየተሻሻለ ነው። አሁን ጉሮሮዬ እላይኛው ክፍል ላይ ብቻ ነው ያለው። እንዲያውም በይበልጥ ያለው አፍንጫዬ ላይ ነው። ይሄም የተለመደ የሚጠበቅ ነገር መሆኑን ነገረውኛል። ስለዚህ ሙሉ በሙሉ እያገገምኩ ነኝ። እንደእግዚአብሄር ፈቃድ" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ ለኮቪድ-19 መጋለጣቸው በምርመራ ከታወቀ ጊዜ አንስተው በዋይት ኃውስ ራሳቸውን ከሌሎች ለይተው ነው ያሉት። ፓክሲሎቪድ የተባለውን የጸረ ኮቪድ መድሃኒት እና ጥቂት መጠን ያለው አስፒሪን ለደም ማቅጠኛ ሲወስዱ መቆየታቸው ተገልጿል።

እንደ ዋይት ኃውስ ባለሥልጣናት ዕምነት የፕሬዚደንቱ የኮቪድ-19 ህመም ምልክት ቢኤ 5 የተባለው የኦሚክሮን ቫይረስ ዝርያ ዐይነት ነው። የኋይት ኃውስ የጸረ ኮቪድ-19 ምላሽ አስተባባሪ ዶክተር አሺሽ ጃ እንዳሉት ባሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ካሉት የኮቪድ-19 ተግላጮች ውስጥ ከ75 እስከ 80 ከመቶ የሚሆኑትን የያዛቸው ቢኤ 5 የተባለው የኦሚክሮን ዝርያ ዐይነት ነው።

ቀዳማዊት ዕመቤት ጂል ባይደን ከቫይረሱ ነጻ ሲሆኑ ላልተወሰነ ጊዜ ዴላዌር በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እንደሚቆዩ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG