የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት የያዙበት ሁኔታ “ስህተት ነው” ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ተናገሩ።
ትላንት ማምሻውን በእስራኤል ጉዳይ ላይ አስተያየቸውን የሰጡት ባይደን፣ ተጨማሪ ርዳታ ወደ ጋዛ መላክ ይቻል ዘንድ የተኩስ አቁም እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ባይደን በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ኔታንያሁ በሐማስ ላይ የሚያካሄዱትን ጥቃት በግልፅ ይደግፉ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ግን ትዕግስታቸው እየተሟጠጠና፣ አስተዳደራቸውም በእስራኤል ላይ ጠንከር ያለ አቋም በመያዝ ላይ ነው ሲል የአሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል። ይህም የሁለቱን ሃገራት የረጅም ግዜ ወዳጅነት ያናጋ እና በጦርነቱ ምክንያት በእስራኤል ላይ የሚታየው ዓለም አቀፍ መገለል እየተጠናከረ እንዲመጣ አድርጓል።
እስራኤል የጋዛን ደቡባዊ ከተማ ራፋን ለማጥቃት ዕቅድ መያዟ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ትልቅ አለመስማማትን የፈጠረ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት እስራኤል በፈፀመችው የአየር ጥቃት ምግብ በማከፋፈል ላይ የነበረ ግብረ ሰናይ ድርጅት ዓባላት የሆኑ ሰባት ሰዎች መገደላቸው በባይደን አስተዳደር በኩል ቁጣን ቀስቅሷል።
በዛሬው የኢድ አል ፈጥር በዓል አከባበር፣ ፍልስጤማውያን ፀሎት ካደረሱ በኋላ በጦርነቱ የተገደሉ ወገኖቻቸውን መቃብር ሲጎበኙ ተሰተውሏል።
መድረክ / ፎረም