የዩኤስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከትናንት በስቲያ እሁድ የ26 ሰከንድ ርዝማኔ ባለው የቪዲዮ መልዕክት አርፍደው የቲክቶክ ተጠቃሚ ሆኑ። የፕሬዝዳንቱ የቲክቶክ ተጠቃሚነት ወሬ የተሰማው አጫጭር የቪዲዮ ምስሎች መጋሪያው የማሕበራዊ ትስስር መድረክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአብዛኛው በሪፐብሊካን ፓርቲው ወገኖች እና በባይደን አስተዳደር ጭምር በዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርበት ከቆየ በኋላ ነው።
በቻይናው ኩባንያ ባይት-ዳንስ ንብረት የሆነው ቲክቶክ በበርካታ የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች ‘የቤጂንግ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ነው’ የሚል ክስ ሲቀርብበት የቆየ ነው። ይሁን እንጂ ኩባንያው ውንጀላውን አጥብቆ ያስተባብላል።
በባይደን የምርጫ ዘመቻ ስም የወጣው የእሁዱ ቪዲዮ ከዴሞክራት ፓርቲው ወገን የሆኑት የ81 አመቱ ፕሬዝዳንት ባይደን፡ ከፖለቲካ ነክ ጉዳዮች እስከ የዩናይትድ ስቴትስ እግር ኳስ የፍጻሜ ዋንጫ ውድድር በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ ያላቸውን ሃሳብ በጫወታ ለዛ ሲያነሱ ያሳያል።
ሱፐር ቦል በመባል ከሚታወቀው የውድድሩ የፍጻሜ ጫወታ እና የተለየ ትኩረት ዘንድሮ ለዚያ በተሰየመው ድምጻዊ አሸር በተመራው ከሚስበው የጫወታው አጋማሽ ትርኢት የቱን እንደሚመርጡ ተጠይቀው፣ ‘ጨዋታውን መመልከት’ ብለዋል።
ኮከብ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኟ ቴይለር ስዊፍት ዝነኛነቷን ተጠቅማ ባይደንን ለመጥቀም የጠነሰሰችው ‘ሚስጥራዊ ውጥን አለ’ የሚለውን የቀኝ አጥባቂዎች የሴራ ወሬ አስመልክቶም ለተጠየቁት ”ብነግርህ ችግር ውስጥ እገባለሁ" ሲሉ በጫወታ መልሰዋል።
በእሁዱ ቪዲዮ ማብቂያም በመጭው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መሆኑ ነው “ማንን ይደግፋሉ? ራስዎን ወይንስ የሪፐብሊካን ተፎካካሪ ዶናልድ ትረምፕን?” ለሚለው፤ "ትቀልዳለህ?" ሳቅ ብለው "ባይደን" ብለዋል።
መድረክ / ፎረም