በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ ዜግነት ካላቸው ጋራ ትዳር የፈጸሙ ዜግነት ሊያገኙ ይችላሉ


ፎቶ ፋይል፦የዜግነት ቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ሳንዲያጎ፣ ካሊፎርኒያ እአአ የካቲት 15/2023
ፎቶ ፋይል፦የዜግነት ቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ሳንዲያጎ፣ ካሊፎርኒያ እአአ የካቲት 15/2023

የአሜሪካ ዜግነት የሌላቸው ነገር ግን ወደ አሜሪካ ከመጡ በኋላ ዜጋ ከሆኑት ጋራ በትዳር የተጣመዱ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ብሎም ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅድ ደንብ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ዛሬ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ዋይት ሃውስ እንዳስታወቀው፣ የአሜሪካ ዜጎችን ያገቡ ነገር ግን ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሃገሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ለመኖሪያ ፈቃድ ወይም ግሪን ካርድ ማመልከት ይችላሉ። ቀጥሎም ለዜግነት ማመልከት እንደሚችሉ አስተዳደሩ ጨምሮ አስታውቋል።

የአስተዳደሩ ውሳኔ የመጣው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ሃገሪቱ በድንበር በኩል ሾልከው የሚገቡ ፍልሰተኞች ላይ ጠንካራ ርምጃ መውሰዱን ተከትሎ ነው። ርምጃው የሰብአዊ መብት አቀንቃኞችን እንዲሁም የዲሞክራቲክ ፓርቲው ም/ቤት ዓባላትን ጭምር ያስቆጣ ነበር ተብሏል።

በአዲሱ ደንብ፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በደንቡ መሠረት አመልካቾች በአሜሪካ ለ10 ዓመት የኖሩ እና የአሜሪካ ዜግነት ካለው ሰው ጋራ ትዳር የፈጸሙ መሆን አለባቸው። ማመልከቻቸው ተቀባይነት ካገኘም፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ለቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ግሪን ካርድ ማመልከት እንደሚችሉ ታውቋል። በተጨማሪም ጊዜያዊ የሥራ ፈቃድ የሚያገኙ ሲሆን፣ ወደ ሃገራቸው ከመባረርም እንደሚድኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ የአሜሪካ ዜግነት የሌላቸው፣ ነገር ግን የአሜሪካ ዜግነት ካለው ሰው ጋራ ትዳር የፈፀመ ወላጅ ያላቸው ልጆችም የተመሳሳይ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

ባይደን ዛሬ ማክሰኞ በዋሽንግተን የሰዓት አቆጣጠር ከቀትር በኋላ ላይ ዋይት ሃውስ ውስጥ በሚካሄድ ሥነ ስርአት ስለ እቅዳቸው ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG