በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ለእንቁጣጣሽ በዓል የፕሬዚዳንት ጆዜፍ አር ባይደን ጁኒየር መልዕክት”


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

“ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝብ እንዲሁም በመቶ ሺሆች የምትቆጠሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ውርስ ያላችሁ አሜሪካዊያንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ነገ እንቁጣጣሽን ለምታከብሩ ሁሉ ጂል እና እኔ የላቀ ምኞታችንን እና መልካም አዲስ ዓመት እንመኝላችኋለን” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በራሳቸውና በባለቤታቸው ስም ማምሻውን መልዕክት አስተላልፈዋል።

“ለእንቁጣጣሽ በዓል የፕሬዚዳንት ጆዜፍ አር ባይደን ጁኒየር መልዕክት” በሚል ርዕስ በዋይት ሀውስ ቤተመንግሥት ዌብ ሳይት ላይ በወጣው መልዕክታቸው “ኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያንና ኤርትራዊያን አሜሪካዊያን በመላ ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ማህበረሰቦችን በማበልጸግ በሃገራችን የየዕለት ህይወት እያንዳንዷ ገፅታ ላይ ቁልፍ ናችሁ” ብለዋል ባይደን።

“ለብዙዎቻችሁ ያለፈው ዓመት ከባድ እንደነበር አውቃለሁ” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። “ኮቪድ 19 ካደረሰው መጎዳትና ማጣት ጋር ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት ቤተሰቦቻችሁንና የምትወድዷቸውን ሁሉ እየጎዳ መሆኑን አውቃለሁ” ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን ኢትዮጵያ ውስጥ በሲቪሎች ላይ እየደረሰ ነው ያሉት ጥቃት በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል።

አፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉ ግጭቶች ሁሉ ወደ ሰላማዊ መፍትኄ እንዲያመሩ አስተዳደራቸው በመላ አካባቢው ካሉ አጋሮች ጋር የነቃ የዲፕሎማሲ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ባይደን አስታውቀዋል።

“እንደ ኢትዮጵያና ኤርትራ የዳያስፖራ አባላት በአካባቢው ሰላምና ብልፅግና እንዲጠናከሩ ብዙዎቻችሁ በቀጥታ እያበረከታችሁ ያለውን አስተዋፅዖ እገነዘባለሁ፤ አደንቃለሁም” ብለዋል ፕሬዚዳንት ባይደን።

ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪካ ቀንድ ህዝብ ጥቅልና የረዥም ጊዜ የወዳጅነት ቁርጠኛነት እንዳላት ፕሬዚዳንቱ አመልክተው። በየትኛውም የሕዝብ ቡድን ላይ የሚፈፀምን ኢሰብዓዊ ጥቃት መቃወማችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

በአካባቢው ለሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎቶችም ምላሽና ድጋፍ መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ ፕሬዚዳንት ባይደን አክለው አስታውቀዋል።

“ታላቋና ኅብረ-ስብጥሯ ኢትዮጵያ አሁን የተደቀኑባትን የመከፋፈል አደጋዎች እንደምታሸንፍና በድርድር የሚደረስበትን ተኩስ ማቆም ጨምሮ እየተካሄደ ላለው ግጭት መፍትኄ እንደምታበጅ እናምናለን” ብለዋል ፕሬዚዳንት ባይደን በዚሁ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው።

“ሰላምን መገንባት ቀላል አይደለም” ብለዋል ባይደን ይሁን እንጂ በውይይትና በሰብዕናችን ውስጥ አንድነትን በመሻት ወይም በመፈለግ ዛሬ ሊጀመር ይችላል፤ መጀመር አለበት” ሲሉ ጉትጎታቸውን አጠናክረዋል።

በአማርኛ ቃላት “መልካም አዲስ ዓመት” ብለዋል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዓሉን ለሚያከብሩ ሁሉ። “ይህ ዓመት ሰላምና እርቅ የሚወርድበት በመላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ እንዲሁም በመላው ዓለም፤ ቤተሰቦችና ማኅበረሰቦች ፈውስ የሚያገኙበት እንዲሆን እፀልያለሁ” ሲሉ ባይደን ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የአዲስ ዓመት የእንቁጣጣሽ የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ደምድመዋል።

XS
SM
MD
LG