ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚገኝ የትኛውም ክትባት ደኅንነቱና የሚሰራ መሆኑ መረጋገጥ ያለበት በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ሳይሆን በሳይንቲስቶች ቦርድ ነው ሲሉ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዲሞክራቱ ተፎካካሪ ጆ ባይደን አሳሰቡ።
የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ይህን ያሉት ዴላዌር ዊልሚንግተን ከተማ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ነው።
"እኔ በክትባት አምናለሁ፣ ሳይንቲስቶችንም አምናቸዋለሁ ዶናልድ ትረምፕን ግን አላምናቸውም፤ በዚህ ሰዓት የአሜሪካ ህዝብም ሊያምናቸው አይችልም" ብለዋል።
ክትባቱ በሚወጣበት ጊዜ ለህዝብ የሚዳረስበት ቅድሚያ የሚሰጣቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አያያዙን እና አቀማመጡን በተመለከተ ባይደን ያሰናዱትን ዕቅድም አብራርተዋል።
ቫይረሱ የጊዜ ሰሌዳ እንደማይከተል ሁሉ በሳይንሳዊ ምርመር የሚገኙ ስኬቶች ጊዜ እየጠበቁ አይመጡም፤ ፈጽሞ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን በመከተል አይሰሩም። ክትባት የሚሰራበት ፈቃድ የሚያገኝበት እና ለህዝብ የሚከፋፈልበትም ሥራ ለፖለቲካ ተብሎ መጣመም የለበትም ብለዋል።
ባይደን ይህን ካሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፕሬዚደንት ትረምፕ በዋይት ኃውስ በሰጡት ቃል ተፎካካሪያቸውን በኔ ፕሬዚዳንትነት የወጣ ክትባት ስለሚከፋፈልበት መንገድ ዕቅድ ማውጣት የለባቸውም ብለዋል።
ያገኘነው እኛ ነን፤ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ይፋ እናደርገዋለን የመጀመሪያው ክትባት በሚመጣው ጥቅምት ወር ዝግጁ ይሆናል ሲሉ ተንብየዋል፥ እስከዚህ የፈረንጆች 2020 መጨረሻ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አንድ መቶ ሚሊዮን ክትባቶችን ለማቅረብ ተዘጋጅቱዋል ሲሉም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።