ለዩክሬን ድጋፍ ለማድረግ የተጠየቀውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እርዳታ ለማግኘት እና በአሜሪካ መንግሥት ላይ እያንዣበበ ያለውን የመዘጋት ስጋት ለማስወገድ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ የምክርቤት አመራሮችን በዋይት ኃውስ ጠርተው ሊያነጋግሩ ነው።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ብዙኃን መሪ ቻክ ሹመር፣ የሪፐብሊካኖች መሪ ሚች ማኮኔል፣ የተወካዮች ምክርቤቱ አፈጉባዔ ማይክ ጆንሰን እና በምክርቤቱ አናሳ ድምፅ ያላቸው ዲሞክራቶች መሪ ሀኪም ጄፍራስ በውይይቱ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በዲሞክራት የሚመረው የሕግ መወሰኛው ምክርቤት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የ95 ቢሊየን ዶላር የፀጥታ ረቂቅ አዋጅ ያፀደቀ ሲሆን፣ 61 ቢሊየን ዶላር ለዩክሬን፣ 14 ቢሊየን ዶላር ለእስራኤል እና ወደ 5 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ደግሞ ታይዋንን ጨምሮ በህንድ ፓስፊክ አካባቢ ለሚገኙ አጋሮች የሚሰጥ ድጋፍን ያካታትታል።
ሆኖም ሪፐብሊካኑ ጆንሰን፣ የአሜሪካ ሕዝብ የሚፈልገው የሕግ አውጪ አካላት ገንዘብ ወደ ውጪ እንዲልኩ ሳይሆን፣ የድንበር ጥበቃን ጨምሮ በአገር ውስጥ ችግሮች ላይ እንዲያተኩሩ ነው በማለት፣ ረቂቁን ድምፅ ለማሰጠት ወደ ምክርቤቱ እንደማይወስዱ ተናግረዋል።
ሹመር በበኩላቸው ዩክሬንን አለመደገፍ አጋሮች በዩናይትድ ስቴትስ ላይ መተማመን እንደማይችሉ ያሳያል ሲሉ ማክሰኞ እለት ተናግረዋል።
መሪዎቹ ግብርናን፣ ትራንስፖርት እና ለቀድሞ ወታደሮች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጨምሮ፣ ለአንዳንድ የመንግስት አካላት የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፎች ላይ ለመስማማት የቀራቸው ጊዜ እስከ መጪ አርብ ድረስ ብቻ ነው። ከአንድ ሳምንት በኃላ ደግሞ ለቀሪው የመንግስት አካል የሚሰጠውን በጀት ለማፅደቅ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ያበቃል።
መድረክ / ፎረም