ካንሰር ዕጢዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስወገድ የሚረዳ ቴክኖሎጂን ለማበልጸግ ይውል ዘንድ ተጨማሪ 150 ሚሊዪን ዶላር የፌዴራል መዋዕለ ነዋይ መመደቡን ፕሬዝደንት ባይደን ትላንት አስታውቀዋል።
ገንዘቡ በአሜሪካ ላሉ የካንሰር ምርምር ተቋማት የሚውል ሲሆን፣ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች የካንሰር ዕጢን በተሻለ መንገድ ማስወገድ እንዲችሉ የሚረዳ ቴክኖሎጂን ለማበልጸግ የሚውል እንደሆነ ፕሬዝደንቱ አመልክተዋል።
በኒው ኦርሊየንስ ቱሌን ዩኒቨርስቲ የሚገኘውን የካንሰር ምርምር ክፍልን የጎበኙት ባይደን፣ አበረታች ውጤት ማየታቸውንና ሐኪሞች ሌሎች የውስጥ ሰውነት ክፍሎችን፣ ነርቮችና የደም ሥርን ሳይጎዱ የካንሰር ዕጢውን ማሰወገድ የሚችሉበትን ሁኔታ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
በፕሬዝደንት ባይደንና በቀዳማዊ እመቤት ጂል ባይደን የሚመራውና “ካንሰር ሙንሻት” በሚል የሚጠራው ፕሮግራም፣ በእ.አ.አ 2047 በአሜሪካ በካንሰር ሳቢያ የሚከሰተውን ሞት በግማሽ ለመቀነስ ያለመ ነው።
ፕሮግራሙ በሁለት የመጀመሪያው ዓመታት 400 ሚሊዮን ዶላር ለካንሰር ምርምር መመደቡንና ይህም ካንሰርን ለመመርመር፣ ለመከላከል እና ለማከም እንደሚውል ዋይት ሃውስ አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም