በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን 4 ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር የትምህርት ዕዳ ሠረዙ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በሥልጣን ዘመናቸው የመጨረሻ አንድ ወር ውስጥ ባሉበት በዚህ ወቅት 4 ነጥብ 28 ቢሊዮን ዶላር የከፍተኛ ትምህርት ዕዳ ሠርዘዋል።

በዕዳ ሥረዛው ተጨማሪ 55 ሺሕ አሜሪካውያን፤ በተለይም መምህራን፣ ነርሶች፣ የሠራዊት አባላት፣ በደኅንነትና ፀጥታ መስክ እንዲሁም ማኅበረሰቡን በሚያገለግሉ መስኮች የተሠማሩ አሜሪካውያን ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በባይደን አስተዳደር ዘመን አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ አሜሪካውያን ለከፍተኛ ትምህርት ክፍያ የገቡት ዕዳ ተሠርዞላቸዋል።

ከፍተኛ ትምህርት አሜሪካውያንን ለዕዳ የሚዳርግ ሳይሆን ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ የሚያሻግራቸው እንዲሆን ለመሥራት በአስተዳደራቸው ዘመን መጀመሪያ ላይ ቃል መግባታቸውን ባይደን አስታውሰዋል።

በባይደን የአራት ዓመታት አስተዳደር በአጠቃላይ 180 ቢሊዮን ዶላር የከፍተኛ ትምህርት ዕዳ መሠረዙንና ይህም አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ አሜሪካውያን የተሻለ ኑሮ እንዲኖራቸው ማስቻሉን የትምህርት ሚንስትሩ ሚጌል ካሮና ዛሬ ዓርብ ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

ዲሞክራቱ ፕሬዝደንት በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የትምህርት ዕዳ ለመሰረዝ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ከፍተኛ የዕዳ ስረዛ መርሐ ግብር ለመጀመር ወስነው እንደነበር ሲታወስ፣ ፕሮግራሙ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ አንዳንድ ተበዳሪዎች እስከ 20 ሺሕ ዶላር ዕዳ እንዲሰረዝላቸው ሊያደርግ ይችል እንደነበር፤ ለሌሎች ደግሞ እስከ 10 ሺሕ ዶላር እንዲሰረዝላቸው ሊያደርግ ይችል እንደነበር ተመልክቷል።

በወግ አጥባቂ ዳኞች ተጽዕኖ ሥር ያለው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛው የገንዘብ መጠን "ፕሬዝደንቱ የሥልጣናቸውን ገደብ ማለፋቸውን ያመለክታል" በሚል ዕቅዱን ውድቅ አድርጎታል።

በፒው የጥናት ተቋም መረጃ መሠረት ከአራት አሜሪካውያን አንዱየከፍተኛ ትምህርት ዕዳ ያለባቸው ሲሆን፣ የዕዳውም መጠን እንደ ትምህርቱ ደረጃ በአማካይ ከ20 እስከ 25 ሺሕ ዶላር ይሆናል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG