ዋሺንግተን ዲሲ —
ሃምሳ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ መድረክ የቆዩት የቀድሞ ምክትል ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የዲሞክራቲክ ፓርቲያቸውን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩነት ትናንት ሃሙስ ማታ በይፋ ተቀብለዋል።
እኤአ ህዳር ሦስት በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የአሜሪካ ህዝብ ሪፖብሊካኑ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከአንድ የሥልጣን ዘመን እንዳያልፉ ማድረግ አለበት ብለዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አላባራ ባለበትና ብዙ ሚሊዮን ህዝብ ለሥራ አጥነት በተዳረገበት በአሁኑ ወቅት ባይደን በትናንቱ የፕሬዚዳንታው ዕጩነት መቀበያ ንግግራቸው
“በአንድነት ሆነን አሜሪካን የሸፈናትን ጨለማ ልናሸንፈው እንችላለን፣ እናሸንፈዋለንም" ብለዋል።
ስለወረርሽኙ መዛመት ትረምፕ ኃላፊነት አልወስድ ብለዋል። ትግሉን ለመምራትም ፈቃደኛ አይደሉም ሲሉ ጆ ባይደን ወቅሰዋል።