በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን ለመጪው የትረምፕ አስተዳደር የብሔራዊ ጸጥታ ማስታወሻ ሰነድ አዘጋጁ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለመጪው የትረምፕ አስተዳደር በቻይና፣ ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ መካከል እያደገ ያለውን ትብብር ለመመከት እንደ ፍኖተ ካርታ ሊያገለግል የሚችል አዲስ የብሔራዊ ደህንነት ማስታወሻ አዘጋጁ።

ዶናልድ ትረምፕ በመጭው ጥር ሥልጣን ከመረከባቸው በፊት ማስታወሻው መዘጋጀቱን ያረጋገጡት በኋይት ሀውስ ደንብ መሠረት ስማቸውን ያልገለጹ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡

የማስታወሻው ዓላማ ትረምፕ ሥልጣን ከተረከቡበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ የአሜሪካ ቀንደኛ ባላንጣና ተቀናቃኝ የሆኑትን ሀገራት ግንኙነቶች በሚመለከት አስተዳደራቸው ከወዲሁ እንዲዘጋጅ ለመርዳት እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የማስታወሻው ሰነድ አራት ሰፋፊ ምክረ ሃሳቦችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የአሜሪካ የመንግሥት ተቋማት ትብብርን ማሻሻል፣ ስለ ባላንጣዎቹ መረጃዎችን ለአጋሮች የማጋራቱን አሠራር ማፋጠንን ይጨምራል። እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀቦችና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ርምጃዎችን ውጤማነት ማሳደግ፣ እና በአንድ ጊዜ ባላንጣዎቹ የተሳተፉባቸው የተለያዩ ቀውሶች ሲከሰቱ ለማስተናገድ ዝግጁነትን ማጠናከር የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ በአራቱ አገሮች መካከል ያለው ትብብር ለብዙ ዓመታት ሲያሳስባት ቆይቷል። በሀገራቱ መካከል ያለው ትብብር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ መፋጠኑ ተመልክቷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት ሩሲያ በብዙ የዓለም ክፍሎች እየተገለለች በመሄዷ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) እና ሚሳይሎች ፍለጋ ፊቷን ወደኢራን አዙራለች። ከሰሜን ኮሪያ መድፎች እና ሚሳይሎችን ተቀብላለች፡፡ በኩርስክ ክልል የዩክሬይን ኃይሎችን ለመመከት የሩሲያን ወታደሮች የሚያግዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ሳይቀሩ ከሰሜን ኮሪያ ተጉዘዋል፡፡

ቻይና በበኩሏ ለወታደራዊና ሲቪል ድርብ ጠቀሜታ ያላቸውን ድጋፎች በመስጠት የሩሲያ ወታደራዊ ኢንዱስትሪ እንዲቀጥል አግዛለች፡፡

ሩሲያም በምላሹ የሚሳይል መከላከያ እና የጠፈር ቴክኖሎጂዋን ለማጠናከር ተዋጊ ጄቶችን በመላክ ቴህራንን ረድታለች።

ሰሜን ኮሪያም የማምረቻ እና ወታደራዊ አቅሟን ለመገንባት የሚያግዝ እንዲሁም እጅግ የሚያስፈልጋትን ነዳጅ እና የገንዘብ ድጋፍ ከሩሲያ ተቀብላለች።

ሩሲያ "ሰሜን ኮሪያን እንደ ኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሀገርነት ተቀብላለች"ሲሉም ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል፡፡

ቻይና እና ሩሲያ ወታደራዊ የቴክኒክ ትብብራቸውን ለማጠናከር በጋራ የሚሠሩ ሲሆን ቻይናውያን ከሩሲያ ዕውቀት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። ሁለቱ ሀገራት በአርክቲክ ክልል የጋራ ጥበቃ እያደረጉ ነው።

ባይደን እና ትረምፕ በጣም የተለያዩ የዓለም አተያዮች ቢኖሯቸውም፣ በመጪው እና በወጪው አስተዳደሮች ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት፣ በሽግግሩ ወቅት በብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች ላይ መተባበር እንደፈለጉ ተናግረዋል ።

ከባለሥልጣናቱ አንዱ የባይደን የኋይት ሀውስ ማስታወሻ “የትረምፕ አስተዳደርን ከምክረ ሃሳቦቹ እንዳይወጣ ለመገደብ ወይም ወደ ሌላ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዳያጋድል ለማድረግ የታለመ አይደለም” ብለዋል።

ባለሥልጣኑ “ሰነዱ መጪው አስተዳደር ሊያጋጥሙት በሚችሉ በጣም አስቸጋሪ የውጭ ፖሊሲዎች ላይ ፖሊሲውን ሲቀርጽ ከወዲሁ አቅም እንዲገነባ ለመርዳት እየታሰበ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG