በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩክሬኑ ጦርነት ሁለተኛ ዓመት ዩናይትድ ስቴትስ በሩስያ ላይ 500 አዳዲስ ማዕቀቦች ጣለች


የዩኤስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
የዩኤስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

ማዕቀቡ ከናቫልኒ እስራት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች፣ የሩስያን የፋይናንስ ዘርፍ፣ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ተቋማት፣ የግዥ ክንውን እውን የሚደረግባቸው አውታሮች እና እንዲሁም በተለያዩ አህጉሮች ውስጥ ቀደም ሲል የተጣሉ ማዕቀቦችን ለማስመለጥ በሚረዱ ወገኖች ላይ የተነጣጠረ መሆኑ ታውቋል።

“ፑቲን በውጭ አገራት ለፈጸሟቸው ጠብ አድራጊ ድርጊቶች እና በአገር ውስጥ ለሚያደርሱት ጭቆና ብርቱ ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው” ሲሉ ባይደን የማዕቀቦቹን ክብደት አመልክተዋል።

በእስር ላይ ሳለ ባለፈው ሳምንት ለሕልፈት የተዳረገውን የሩስያውን የተቃዋሚ መሪ ናቫልኒ’ን ባለቤት ዩሊያ ናቫልንያ እና ሴት ልጃቸው ዳሻ’ን ትላንት ሃሙስ ከዩናይትድ ስቴትሷ የካሊፎርኒያ ክፍለ ግዛት ውስጥ አግኝተው ያነጋገሩት ፕሬዝዳንት ባይደን “ሙስናን በመዋጋት እና ነፃና ዲሞክራሲያዊት ሩስያ እንትፈጠር ታላቅ ቆራጥነት ያሳዩ” ሲሉ ናልቫኒን አወድሰውታል።

ባይደን በዛሬው ዕለት ዩናይትድ ስቴትስ በሩስያ ላይ የጣለቻቸውን አዳዲስ ማዕቀቦች ይፋ ባደረጉበት ወቅት ባሰሙት ንግግራቸው ዩክሬናውያን ነፃነታቸውን እና የወደፊት ዕጣቸውን ለማስጠበቅ ያሳዩትን ቁርጠኝነትም አወድሰዋል። “ኔቶ ይበልጥ ጠንካራ፣ ግዙፍ እና ይበልጥም አንድነት ያለው ድርጅት ሆኗል” ሲሉ “ካሁን ቀደም ያልታየ” በማለት ህብረቱ አለበት ያሉትን ሁኔታ ገልጸዋል።

ሃምሳ ሀገራት ያሉበት ዩክሬይንን የሚደግፈው በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ጥምረት ለዩክሬን ወሳኝ እርዳታ መስጠት እና ሩስያን ለፈጸመችው ወረራ ተጠያቂ ለማድረግ አሁንም በቁርጠኝነት ይቀጥላል ብለዋል።

በተያያዘም ዩክሬን የሩስያን ኃይሎች ጥቃት ለመመከት መዋጋቷን በቀጠለችበት ባሁኑ ወቅት፡ በገጠማት የአቅርቦቶች እጥረት የተነሳ የጦር መሳሪያ እና ጥይት በራሽን እየሰጠች መሆኗ ለተነገረው ኪየቭ፡ ጊዜው ሳያልፍ የማሟያ በጀት እንዲፈቅድ ባይደን የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት በሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች የተሰናዳውን የብሄራዊ ደህንነት ሕግ እንዲያጸድቅ ሲሉ አሳስበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG